ከተማዋ ለማመንጨት የምትችለውን ገቢ በላቀ ደረጃ ለመሰብሰብ ፍትሃዊ የገቢ አሰባሰብ ስርዓት ማስፈን ይገባል ተባለ

You are currently viewing ከተማዋ ለማመንጨት የምትችለውን ገቢ በላቀ ደረጃ ለመሰብሰብ ፍትሃዊ የገቢ አሰባሰብ ስርዓት ማስፈን ይገባል ተባለ

AMN- ታህሳስ 05 / 2017 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የአምስት ወራት ዕቅድ አፈፃጸሙን ገምግሟል፡፡

በመድረኩ የቢሮው ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ የቢሮው የህዳር ወር የገቢ አፈፃፀም ከመቶ ፐርሰንት በላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የበጀት ዓመቱ የአምስቱ ወራት የዕቅድ አፈፃፀሙም ከ88ነጥብ 81 በመቶ በላይ እንደሆነና ገቢው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ሲነፃፀር በ38 ነጥብ 94 ብልጫ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

በህዳር ወር ለተመዘገበው ውጤት አመራሩና ፈፃሚው በቅንጅት ተናቦ መስራቱ ተጠቃሽ መሆኑን የገለፁት የቢሮው ኃላፊ የማዕከል አመራሮች ቅርንጫፎችን በመከፋፈል ያደረጉት ድጋፍና ክትትል ውጤታማ ነበር ብለዋል፡፡

በመሆኑም በህዳር ወር የነበሩ ጠንካራ የክትትልና ድጋፍ ስራዎች ማስቀጠል እንደሚገባ የገለጹት ኃላፊው የሚጠበቅባቸውን ግብር ያልከፈሉ ታክስ ከፋዮችን ተከታትሎ ለማስከፈል የህግ ማስከበር ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች የሚሰበሰብ ግብር የፍትሃዊነት መርህን መሰረት ማድረጉን ማረጋገጥ ይገባል ያሉት ኃላፊው ገቢ ሊሰበሰብ የሚገባው ፍትሃዊ በሆነ መልኩ በትክክለኛ መረጃ ላይ በመመስረት ሊሆን እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡

አሁንም ለተጨማሪ እሴት ታክስ መመዝገብ እየተገባቸው ያልተመዘገቡ በርካታ ነጋዴዎች መኖራቸውን ያነሱት ኃላፊው በአንፃሩ መመዝገብ የማይገባቸውም የፍትሃዊነት መርህን በሚጥስ መልኩ እንዲመዘገቡ የተደረጉ በመኖራቸው ማረም ይገባል ብለዋል፡፡

የዕዳ ክትትልና አሰባሰብ ተግባራት ፣ ቫት ያላሳወቁ ግብር ከፋዮች እንዲያሳውቁና ክፍያ እንዲፈፅሙ የማድረግ ፣ ፍትሃዊ የገቢ አሰባሰብ ስርዓትን የማጠናከር ተግባር ሊኖር

እንደሚገባ አመልክተዋል ።

የታክስ ውሳኔ ተወስኖ ያልተሰበሰቡ ገቢዎች ትኩረት በመስጠት እንደሚሰበሰቡ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ሌብነትና ብልሹ አሰራሮችን መከላከልና የደረሰኝ የቁጥጥር ስራዎች ማጠናከር በቀጣይ ወራት ትኩረት በማድረግ መፈፀም ይገባል ያሉት አቶ ቢኒያም ለተገልጋዩ ሕብረተሰብ የተሳለጠ አገልግሎት መስጠትና የመስተንግዶ ስራዎች ልዩ ትኩረት እንደሚያገኙም ገልጸዋል ።

የከተማዋን የገቢ አቅም አሟጦ ለመሰብሰብ ከተለመደ አሰራርና የስራ ባህል መውጣት እንደሚያስፈልግ የተገለጸ ሲሆን በህዳር ወር የተጀመረውን አምሽቶ የመስራት የስራ ባህል አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ተብሏል፡፡

ከታክስ አሰባሰብ ጋር በተያያዘም ጥራት ያለውና የተደራጀ መረጃ አያያዝ ስርዓት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ማረም እንደሚገባም ተመልክቷል ፡፡

በቢሮው ከሪሊ ስቴቶች፣ ከኤምባሲዎ፣ከሞሎችና ከኮንስትራክሽን ግብአት አቅራቢዎች ጋር በተያያዘ የገቢ መሰረት ለማስፋት ታቅደው ወደ ተግባር የተሸጋገሩ ተግባራት ወጥ በሆነ ደረጃ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባልም ተብሏል።

ከደረሰኝ ቁጥጥር ጋር በተያያዘም በአስመጪዎች፣ በአከፋፋዮችና በአምራቾች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ተገልጿል።

ከመርካቶ ባሻገር በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች በወጥነት ማስፈፀም እንደሚገባም መጠቆሙን ከአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review