
AMN – ታኅሣሥ 7/2017 ዓ.ም
የሰላም ሰራዊት አደረጃጀት ለተልዕኮ ዝግጁ እንዲሆንና ተለዋዋጭ ለሆኑ የወንጀል ድርጊቶች ተገቢውን ምላሽ መስጠት እንዲችል አቅሙን ማጎልበት ያስፈልጋል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የነባር ሰላም ሰራዊት ብሎክ አመራሮች የንድፈ ሀሳብና የተግባር ማነቃቂያ ስልጠና ማስጀመሪያ መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
ሰልጣኞቹ ከጉለሌ፣ከልደታና ከአራዳ ክፍለ ከተማ የተወጣጡ ናቸው።
በስልጠና ማስጀመሪያ መርሀግብሩ ላይ የተገኙት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ከተማዋ የአፍሪካ መዲናና የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንደመሆኗ ጠንካራ የፀጥታ አደረጃጀት ያስፈልጋታል ብለዋል።
በዚህ ረገድ የሰላም ሰራዊት አደረጃጀት የህግ የበላይነት እና ደህንነትን በማስጠበቅ በኩል ከፍተኛ ድርሻ እየተወጣ ስለመሆኑ አንስተዋል።
የፀጥታ ስራ አንዴ ተሰርቶ የሚቆም ባለመሆኑ ይህ አደረጃጀት ለተልዕኮ ዝግጁ እንዲሆን፣ለተለዋዋጭ የወንጀል ድርጊቶች ተገቢውን ምላሽ መስጠት እንዲችልና ለፀጥታ አካላት አጋዥ እንዲሆን በስልጠና መታገዝ አለበትም ነው ያሉት ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊው አቶ ሚደቅሳ ከበደ በበኩላቸው የሰላም ሰራዊት አባላት ከፀጥታው መዋቅር ጋር በመሆን ከተማዋ ሰላሟ የተጠበቀ እንዲሆን አስተዋፅኦአድርገዋል ብለዋል።
በሰባት መርሀ ግብሮች የሚከናወነው ስልጠና በሰላም ሰራዊት አሰራር ተግባርና ኃላፊነት፣በስነ ምግባርና የስጋት ቦታ ልየታ እና በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩርም ምክትል ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል።
ወታደራዊ የመስክ ስልጠናዎች እንደሚሰጡም ነው በመርሀ ግብሩ ላይ የተጠቀሰው።
በከተማዋ 11ንዱም ክፍለ ከተሞች ከ241 ሺህ በላይ የሰላም ሰራዊት አባላት እንደሚገኙ ተመልክቷል።
በትዕግስት መንግስቱ