መንግሥት የወሰዳቸው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

You are currently viewing መንግሥት የወሰዳቸው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

AMN – ታኅሣሥ 8/2017 ዓ.ም

መንግሥት በለውጡ ዓመታት የወሰዳቸው ሁሉን አቀፍ ማሻሻያዎች የሰለጠነ የፖለቲካ ባህልን ከማዳበር ባለፈ የግሉን ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ያጎለበቱ መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትጵያና የአውሮፓ ህብረትን ትብብር ለማጠናከር ያለመ የስትራቴጂክ አጋርነት መድረክ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡

በመድረኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)፣ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ የፍትህ ሚኒስትር ሀና አርዓያሥላሴ እንዲሁም በአዲስ አበባ የሚገኙ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት አምባሳደሮችና ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ቁልፍ የሰላምና የልማት አጋር መሆኑ በኢትዮጵያ ሀገራዊና ቀጣናዊ ሚና ላይ ለመወያየት እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡

ከአውሮፓ ህብረት አምባሳደሮችና ተወካዮች ጋር የሚደረገው ውይይትም በሰላምና ጸጥታ፣ በኢኮኖሚ ልማትና በባለብዙ ወገን ትብብር ላይ የሚያተኩር መሆኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፍላጎትን ከውይይት ይልቅ በኃይል ለማሳካት የመፈለግ መጥፎ ልምምድ የታሪክ ስብራት ሆኖ መቆየቱን አውስተዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት ስብራቶችን የሚጠግን የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ተደርገዋል ብለዋል።

ለዚህም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፣ የሽግግር ፍትሕ፣ የተሃድሶ ኮሚሽን፣ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲሁም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራውን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

ይህም የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥም ባሻገር የግሉን ዘርፍ የንግድና ኢንቨስትመንት ተሳትፎ ማሳደጉን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረትና አባል ሀገራት ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት ማጠናከር እንደምትፈልግ ገልጸው፤ ትብብሯን ለማጠናከር ዘርፈ ብዙ ጥረት ማድረጓንም ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኢመስበርገር በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ ሚና እንዳላት ተናግረዋል።

የአውሮፓ ህብረትና አባል ሀገራት የኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ጉዳዮች እንደሚጋሩ ጠቅሰው፤ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ትግበራ ባለፉት ሁለት ዓመታት ጥሩ እድገት እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሶማሊያ ጋር የተደረሰው የአንካራው ስምምነት በቀጣናው ሰላምና ደህንነትን ለማስፈን መልካም እርምጃ መሆኑን ገልጸው፤ ህብረቱ ለቀጣናው መረጋጋት ሚናውን እንደሚወጣ ጠቁመዋል።

ውይይቱ በኢትዮጵያና በቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ልማት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ሰላምና ደህንነት እንዲሁም ሽብርተኝነትን በመከላከል ላይ የሚያተኩር መሆኑን ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት ትብብራቸውን ለማጠናከር በፈረንጆቹ በ2016 የስትራቴጂክ አጋርነት ትብብር ተፈራርመዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review