ኢትዮጵያ እንደ አገር የገቢ እና የወጪ ንግድ እንቅስቃሴዋ ሚዛኑን የጠበቀ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፣ ወደ ውጪ ከምትልካቸው ምርቶች ይልቅ ወደ አገር ውስጥ የምታስገባቸው ምርቶች በዓይነትም ሆነ በመጠን ይበልጣሉ፡፡ ለዚህ የወጪ እና የገቢ ንግድ ምጣኔ መለያየት ምክንያት ተብለው ከሚጠቀሱት ጉዳዮች መካከል አንዱ የአገር ውስጥ ምርቶችን ዓለም አቀፍ መመዘኛን ባሟላ ሁኔታ የጥራት ደረጃቸውን አለማስጠበቅ እንደሆነ በምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ተደጋግሞ ሲነገር ቆይቷል። መንግስትም ጉዳዩን በመረዳት ለመፍትሄው የሚጠበቅበትን በማድረግ፤ ለችግሩ መፍቻ የሚሆን ቁልፍ ተቋማዊ መሰረተ ልማት በመገንባት ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡
ይህ ተቋም “የጥራት መንደር” ይባላል። በአዲስ አበባ ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው የጥራት መንደር፤ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ መስክ ላይ ጉልህ ሚና መጫወት የሚችል የመሠረተ ልማት ፕሮጀክት እንደሚሆን ይጠበቃል። ለግንባታው 8 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል፡፡ የጥራት መንደሩ የኢትዮጵያ ሥነ- ልክ ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅትን ያካተተ ነው::
የጥራት መንደሩ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱ ኢትዮጵያ በወጪ ንግድ ላይ ያላትን ተሳትፎ ለማሻሻል እና ከዘርፉም የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ የማይተካ ሚና እንደሚጫወት የጠቆሙት የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ቆስጠንጢኖስ በርሄ (ዶ/ር)፤ የተመረቀው የጥራት መንደር የኢንደስትሪ ዕድገትን ለማጎልበት፣ የኤክስፖርት አቅሞችን በማሻሻል ለውጪ ገበያ የሚላኩ ምርቶችን ዓይነትና መጠን ለማሳደግ እንዲሁም የንግድ ቴክኒካል ማነቆዎችን ለመቀነስ ያስችላል። ኢትዮጵያን ከዓለም አቀፍ የእሴት ሰንሰለቶች ጋር በማጣጣም በዓለም አቀፍ ገበያ ንቁ ተሳትፎ እንድታደርግም ያዘጋጃታል ብለዋል።

ምሁሩ አክለው እንዳስረዱት፤ በጥራት መንደር ውስጥ አገልግሎት ለመስጠት ተጣምረው ወደ ሥራ የገቡት ተቋማት ከአገሪቱ የውጪ ንግድ እንቅስቃሴ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ የመንደሩን ውጤታማነት ከፍ ያደርገዋል። የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጪ የሚልኩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ከዚህ ቀደም ይደርስባቸው የነበረውን የአገልግሎት መጓደል ያስቀራል፡፡ ለአላስፈላጊ የገንዘብ፣ የጊዜ እና የጉልበት ብክነት የሚደረጉበትን፣ የተንዛዛ አሠራር፣ ጥራት እና ቅልጥፍና የሌለው አገልግሎትን ይቀርፋል። ፍትሃዊ የተወዳዳሪነት ምህዳርን ያሰፋል። ምርትና ምርታማነትን ያሳድጋል። የሥራ ዕድልን ይፈጥራል። የአገር ኢኮኖሚ እንዲያድግም ትልቅ አቅም ይሆናል፡፡
የጥራት መንደሩ የተቀናጀና ደረጃውን የጠበቀ የጥራት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከምርትና እና አገልግሎት ጥራት ማስጠበቅ ጋር የተያያዙት ተቋማት በአንድ ማዕከል እንዲገኙ ማስቻሉ ትልቅ አበርክቶ አለው። ይህንን ለመረዳት ተቋማቱ የተቋቋሙበትን ዓላማ እና የሚሰጡትን አገልግሎት በጥቂቱ እንመልከት።
በመንደሩ ከተካተቱት ተቋማት አንዱ፤ የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት (Ethiopian Conformity Assessment Organization-ECAE) ነው፡፡ ይህ ተቋም ምርቶች በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጠበቅባቸውን መስፈርቶች ማሟላታቸውን በመፈተሽ እና በማረጋገጥ የምስክር ወረቀት አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡
ሌላኛው ተቋም የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት (Ethiopian Standards Institute-ESI) ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ምርቶች ከዓለም አቀፍ መስፈርቶች ጋር ለማጣጣም አገራዊ የጥራት ደረጃዎችን ያዘጋጃል፤ ያሰራጫል፤ በሥራ ላይ መዋላቸውንም ይከታተላል፡፡
ከምርት ጥራት እና ተስማሚነት ግምገማ፣ ቁጥጥር እና የሥራ ፍቃድ የምስክር ወረቀት ጋር የተያያዙ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ተግባራቸውን በአግባቡ እና በፍትሃዊነት እየተወጡ ስለመሆናቸው የሚከታተለውና የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ እውቅና አገልግሎት (Ethiopian Accreditation Service (EAS) ተቋም፤ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ወደ ኢኮኖሚው እንዲቀላቀሉ ቁልፍ ሚና የሚጫወተው የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣንም (Ethiopian Technology Authority) የጥራት መንደሩ ወሳኝ አቅሞች በመሆን ተሰይመዋል፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የጥራት መሠረተ ልማት ለዘላቂ ዕድገት መሠረት መሆኑን በመጠቆም እንደአገር ሊኖረው የሚችለውን ተጠባቂ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ መዘርዘራቸው ይታወሳል። እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ የጥራት መንደሩ ለአገልግሎት መብቃቱ ጥራት ያለው ምርትን ወደ ውጭ በመላክ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ያስችላል፡፡ ጥራት ከዜጎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር የተሳሰረ በመሆኑ፤ ደረጃቸውን የጠበቁና ጤናማ ምርቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የጥራት መንደሩ አስተዋፅኦ ወሳኝ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ምርቶች በወጪ ንግድ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ትርጉም ባለው ደረጃ ለውጥ በማምጣት ሂደት ውስጥ የጥራት መንደሩ እጅግ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ሚናን ይጫወታል፡፡ የጥራት መንደሩ ከመሰረተ ልማትነት ባሻገር፤ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን ጅማሮ አብሳሪ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡
ለአገር ውስጥ ፍጆታ፣ ለኢንዱስትሪዎች ጥሬ ግብዓት፣ ለውጪ ገበያ አቅርቦት በመዋል ሰፊውን ድርሻ የሚሸፍነው የግብርናው ዘርፍ መሆኑን ያነሱት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ይንገስ ዓለሙ (ዶ/ር)፤ የጥራት መንደሩ ለአገልግሎት መብቃቱ የኢትዮጵያን የግብርና ዘርፍ ውጤታማነት ለማሳደግ የሚኖረው እገዛ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል። ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ወደ ውጪ ከምትልካቸው ምርቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሱት፡-እንደ ቡና፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የቁም እንሰሳት፣ ሰሊጥ፣ ጫት የመሳሰሉት የአገራችን አርሶ እና አርብቶ አደር ማህበረሰብ በቀጥታ የሚሳተፍባቸው የሥራ ውጤቶቹ ናቸው፡፡ ሆኖም አገሪቷ ካላት አቅም አንፃር ለውጪ ገበያ የሚቀርቡት በዓይነትም ሆነ በመጠን በጣም ሲመዘኑ አነስተኛ ናቸው። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት ከታች ጀምሮ ምርትን በዓይነት፣ በጥራት እና በብዛት የማምረት ሂደት ላይ ያለው ጉድለት ነው፡፡ ይህንን ችግር ለማቃለል አሁን ለአገልግሎት የበቃው የጥራት መንደር የማይናቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡
የምጣኔ ሃብት መምህር እና ተማራማሪው ይንገስ (ዶ/ር) አክለው እንዳስረዱት፤ የጥራት መንደሩ ደረጃውን የጠበቀ የኢንዱስትሪዎች ጥሬ ግብዓት ለማምረት፣ የአገር ውስጥ ምርቶችን እሴት በመጨመር ለውጪ ገበያ ለማቅረብ፣ ያልተሞከሩ እና ያልተጠቀምንባቸውን ዘርፎች ለማየትና ለመጠቀም፣ የውጪ ባለሃብቶችን ለመሳብ ወሳኝ አቅም ሆኖ እንደሚያገለግል በመጠቆም፤ እንደአገር ይህንን እና መሰል ተቋም እስካሁን ባለመኖሩ እንደሚያስቆጫቸው አልሸሸጉም። የጥራት መንደሩ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት
እንዲሰጥ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ፤ መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወደ ክልሎች የሚስፋፉበት ሁኔታ ላይ በቀጣይ መተኮር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያ በወጪ እና ገቢ ንግድ መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ለማጥበብ የተለያዩ ስልቶችን ቀይሳ ስትንቀሳቀስ ቆይታለች፡፡ የተሠራው ሥራም ተስፋ ሰጪ ውጤት በማስገኘት ላይ ስለመሆኑ ኢኮኖሚን በተመለከተ እየወጡ ያሉ መረጃዎች እና ሪፖርቶች ያመላክታሉ። ለአብነት ያክል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)፤ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ሪፖርት ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያና ምላሽ ያነሷቸውን አሃዛዊ መረጃዎች መመልከት ጉዳዩን ለማስገንዘብ ያግዛል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ካነሷቸው ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች መካከል፡- እንደ አገር የውጪ ገበያ (ኤክስፖርት) ተሳትፎ መሻሻሉን የሚያረጋግጥ ይገኝበታል። እንደሳቸው ማብራሪያ ከሆነ፤ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሦስት ወራት ከወጪ ንግድ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ለማስገባት ታቅዶ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ ይህ ገቢ በ2000 በጀት ዓመት እንደ አገር ከተገኘው ዓመታዊ የወጪ ንግድ ገቢ ጋር ሲነፃፀር ብልጫ አለው። ይህንን ማስጠበቅ ከተቻለ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከኤክስፖርት ገቢ ማግኘት ይቻላል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በአገር ውስጥ ያለውን አምራች ኢንዱስትሪዎችን አቅም በማሻሻል ከውጪ የሚገቡ ተኪ ምርቶችን በማምረት ይገባ የነበረውን ምርት መጠን በ1 ነጥብ 3 ከመቶ እንዲቀንስ አድርገዋል። በሦስቱ ወራት ውስጥ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በ6 ነጥብ 4 ከመቶ አድጓል፡፡
በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት በብዛት የማይገኙ የሴራሚክ፣ የባትሪ እና የሶላር ሀይል ማመንጫ መፈተሻ መሳሪያዎችን መፈተሽ የሚያስችሉ ላብራቶሪዎችን ጭምር ያካተተው የጥራት መንደሩ፤ በአገልግሎቱ ከአገር ውስጥ አልፎ የጎረቤት አገራትንም ለመጥቀም እንደሚያስችል ተነግሮለታል፡፡ ተጠባቂው የጥራት መንደሩ አስተዋፅኦ ማረፊያው ለሆነችው አዲስ አበባም ከተሜነትን በቃኘ አግባብ እጅግ የበዙ ትሩፋቶችን የሚሰጣት ይሆናል፡፡ መዲናዋ ለነዋሪዎቿ እና ለእንግዶቿ ምቹ ለመሆን፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሁሉን አቀፍ አገልግሎት ለመስጠት፣ የስማርት ከተማነትን ጉዞ በውጤታማነት ለማሳካት … ቀን ከሌሊት ያለማቋረጥ ግዙፍ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲሠሩ እየተደረገ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የጥራት መንደሩ አገልግሎት እጅግ አስፈላጊ ያደርገዋል፡፡
የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ቆስጠንጢኖስ በርሄ (ዶ/ር) እንዳብራሩት፤ የጥራት መንደሩ በከተማዋ የሚገነቡ አስፋልት መንገዶች፣ የእግረኛ መንገዶች፣ አረንጓዴ ቦታዎች እና የመኖሪያ ቤቶች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ያግዛል፡፡ የኤሌክትሪክ፣ የስልክ፣ የውሃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቅንጅታዊ አሠራራቸው እንዲጠናከር ዕድልን ይፈጥራል፡፡ አገልግሎታቸው እንዲዘምን ያደርጋል። የዓለም ጤና ድርጅት መስፈርትን ያሟሉ፣ ጥራት ያላቸው እና ለነዋሪዎቻቸው የተመቹ አካባቢዎች በከተማዋ እንዲስፋፉ በማድረግ የተጀመረው ሥራ ውጤታማ እንዲሆን ያግዛል፡፡ ቴክኖሎጂን እና ስማርት ከተማን ማቀናጀት በመሰረተ ልማት አቅርቦት እና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ጉልህ አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት አቅም ይሆናል፡፡
በኢትዮጵያ በአዲስነቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአገልግሎት የበቃውን “የጥራት መንደር” ዓይነት ግዙፍ መሰረተ ልማትን ገንብቶ ለአገልግሎት ማዋል በሌሎች አገራት የተለመደ ነው። ይህንን ተግባር ቀድመው የጀመሩ እና ልምድ ያደረጉ አገራት ለዛሬው ዕድገታቸው መፋጠን የኃይል ምንጭ ሆኖ አገልግሏቸዋል። ለማሳያነት ያክል የሲንጋፖርን፣ የህንድን እና የጀርመንን ተሞክሮ በጥቂቱ ብንመለከት የኢትዮጵያን የጥራት መንደር ተጠባቂ ዘርፈ ብዙ ውጤት መገመት እንችላለን።
ሲንጋፖር
ሲንጋፖር በርካቶች አዳጊ እና በማደግ ላይ ያሉ አገራት በተምሳሌትነት የሚጠቅሷት አገር ነች። ጠንካራ የምርት ጥራት እና ደረጃ ማስጠበቂያ ስርዓትን ተግባራዊ አድርጋለች። በዚህም የውጭ ንግድ ተወዳዳሪነቷን አሳድጎላታል፡፡ የትላልቅ እና ታዋቂ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች መዳረሻ አድርጓታል፡፡ በጎርጎሮሳዊያን የዘመን ቀመር 2022 ወደ ውጭ ከላከቻቸው ምርቶች ያገኘችው ገቢ ለጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርቷ (GDP) ዕድገት የ174 በመቶ አስተዋፅዖ ማድረጉን በ2023 የወጣው የኤሲያ ልማት ባንክ (Asian Development Bank) መረጃ ያመላክታል። በሲንጋፖር ከሚመረቱ ምርቶች መካከል 98 ከመቶ ያክሉ የ ISO standards ያሟሉ ናቸው፡፡
ህንድ
በአገረ ህንድ የብሔራዊ እውቅና የምስክር ወረቀት አካላት ቦርድ (National Accreditation Board for Certification Bodies-NABCB) እና የህንድ ደረጃዎች ቢሮ (Bureau of Indian Standards -BIS) በዓለም አቀፍ ደረጃ በጥራታቸው ተወዳድረው መመረጥ የሚችሉ ምርቶችን ለማምረት ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ ተቋማት ናቸው፡፡ ይህ መሆኑ ህንድ በአሁኑ ወቅት እንደ ፋርማሲዩቲካል እና ጨርቃ ጨርቅ ባሉ ዘርፎች በቀዳሚነት እንድትቀመጥ አስችሏታል፡፡ ከእነዚህ ዘርፎች ተመርተው ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች በጎርጎሮሳዊያን የዘመን ቀመር ከ2010 ጀምሮ በየዓመቱ በአማካይ በ15 ከመቶ እንዲያድግ አግዟታል፡፡
የቆዳ ምርቶች ኤክስፖርት ካውንስል (Leather Export Council) በማቋቋም፤ ከቆዳ እና ከቆዳ ውጤቶች ጋር የተያያዙ ምርቶች ላይ የጥራት እና የተስማሚነት ግምገማዎች ግዴታ እንዲተገበሩ በማድረጓ ተጠቃሚ ሆናለች፡፡ የቆዳ እና የቆዳ ውጤቶችን ወደ ውጭ በመላክ በጎርጎሮሳዊያን የዘመን ቀመር በ2010 ያገኘችውን የ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በ2022 ወደ 7 ቢሊዮን ዶላር በማድረስ በእጥፍ ማሳደግ ችላለች። ከዚህ በተጨማሪም ከጥራት ጋር የተያያዙ አገልግሎቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ አስደግፋ መስጠቷ፤ ለውጭ ገበያ ምርት የሚልኩ ግለሰቦች እና ተቋማት በየዓመቱ ያወጧቸው የነበረውን ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ የአስተዳደር ወጪዎችን አስቀርቷል፡፡
ጀርመን
የጀርመኑ ዲአይኤን የደረጃዎች ኢንስቲትዩት (DIN Standards Institute ) የተሰኘው ተቋም አገሪቷ በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪና ተመራጭ ምርቶችን በብዛት እንድታቀርብ ቁልፍ አስተዋፅኦ ሲያደርግ ቆይቷል፤ እያደረገም ይገኛል፡፡ ይህ ተቋም የምርቶችን የተስማሚነት ምዘና አገልግሎቶች በመስጠት በጎርጎሮሳዊያን የዘመን ቀመር በ2020 ብቻ ለጀርመን ኢኮኖሚ ከ15 ቢሊዮን ዩሮ በላይ የሚገመት አስተዋፅኦ ማበርከቱን የዓለም ባንክ መረጃ ያመለክታል፡፡
ጀርመናዊያን ለዓለም ገበያ የሚያቀርቧቸው ምርቶች በጥራት እና በተወዳዳሪነት ደረጃቸው ቀዳሚ እንዲሆኑ በትኩረት ይሠራሉ፡፡ አነስተኛ የአምራች እና የንግድ ድርጅቶች እንዲያድጉ፣ ፍትሃዊ የንግድ ውድድር እንዲፈጠር እንዲሁም ለውጪ ንግድ ዝግጁ እንዲሆኑ ተከታታይነት ያለው እገዛ እና ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደ ዲአይኤን የደረጃዎች ኢንስቲትዩት (DIN Standards Institute) ያሉ ተቋማት ቁልፍ ሚናን ይጫወታሉ፡፡
በአዲስ አበባ እየታየ ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ እና ዕድገት የኢትዮጵያን አራቱም አቅጣጫዎች የማዳረስ አቅም እንዳለው የኢትዮጵያ ከተሞች እንቅስቃሴ ምስክር ናቸው፡፡ ይህ ሥራ ከከተሞች አልፎ ሁሉም ገጠሮች፣ መንደሮች፣ ቤቶች ተስፋፍቶ እንዲታይ ከዚህም በላይ በውጤት የታገዘ ጥረት እና ትጋት ይጠይቃል። ሥራው እና ውጤቱ ትውልድ ተሻጋሪ፣ እሴትን አሳዳጊ፣ ድንበር የማይገድበው ማድረግ ከዛሬው ትውልድ ይጠበቃል። ለዚህ ደግሞ ሥራዎችን ከመከወን ባሻገር ለሥራዎቹ እና ለውጤታቸው ጥራት እና ተወዳዳሪነት የሚሰጠው ትኩረት ወሳኝ ነው፡፡ የጥራት ጉዳይ በአንድ ሌሊት ምኞት ወይም በአንድ ወገን ጥረት አይመጣም። ለጥራት እያንዳንዱ ኃላፊነት አለበት። ጥራት የመወዳደሪያ መስፈርት መሆኑን መረዳትና የማይደራደሩበት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ ጥራት በግብርና፣ በማምረቻ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ፣ በሸማች፣ በነጋዴ፣ በአስመጪ፣ በላኪ፣ በተቆጣጣሪ በመሳሰሉ ዘርፎች የተሠማሩ ተቋማት፣ ድርጅቶች፣ ኢንዱስትሪዎች እና ግለሰቦች ቁልፍ ጉዳይ ሊሆን ይገባል፡፡ የጥራት ጥያቄ ጥራት ያለው አገራዊ ምላሽ እንዲያገኝ ደግሞ በቅርቡ ለአገልግሎት የበቃው ኢትዮጵያዊው የጥራት መንደር የአንበሳውን ድርሻ ሊወጣ ይገባል፡፡
በደረጀ ታደሰ