
AMN-ታህሣሥ 13/2017 ዓ.ም
የተጀመሩ ልማቶችን በማሳለጥ ሌብነት እና ብልሹ አሰራርን የመታገል ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተሞች የልማት ፍላጎት ከህዝብ የሚመነጭ መሆኑን የገለፀ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማም እየለሙ ያሉ አካባቢዎች ልማትም ህዝቡ በባለቤትነት ልማቱን ተቀብሎ ከአስተዳደሩ ጎን በመሰለፉ በባለቤትነት በመያዙና በመሳተፍ የከተማዋን ታሪክ የለወጡ ሥራዎች መተግበር ችለዋል ብሏል።
“የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች ከተማችንን ነባሩን ከዘመኑ ጋር ያጣመረ፣ ታሪክን ከአዲሱ ትውልድ ጋር ያጋመደ፣ በወል እውነት የወል ታሪክ የሆነ የከተማዋን ተመራጭነት ከፍታን የሚያጎናጽፍ በአጭር ጊዜ ሀገርን መገንባት እንደሚቻል ያሳየ ህያው ምስክር ሆኗል” ሲልም ገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዜጎችን ማህበራዊ መስተጋብር የሚያስተሳስርና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ የልማት መርህ በመመራት ቃልን በተግባር የሚያስመሰክር ዘላቂ የሆነ ሁለንተናዊ የብልጽግና ተምሳሌትነትን የሚያረጋግጥ 2ኛ ዙር የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶችን እያፋጠነ እንደሚገኝ ከተማ አስተዳደሩ አስታውሷል።
የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በጠበቀ መልኩ በተለይም የመሰረተ ልማት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ተነሽ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ከነበረባቸው ማህበራዊ ጫናዎች ተላቀው እራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት የተሻለ የመኖሪያና የስራ ከባቢ ተፈጥሮላቸዋል ነው የተባለው።
አስተዳደሩ የዜጎችን የእለት ተለት የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ረገድ እየሰራ ያለው ተግባር በተለይ በአዲስ አበባ የዜጎችን ህይወት ከመቀየር አንፃር ጠቀሜታው እያደገ መጥቶ ለሌሎች ክልሎችም ተሞክሮ በመሆን ነዋሪውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ማድረጉን መቀጠሉ ተገልጿል።
እንደ አዲስ አበባ ያሉ ሚሊዮኖች የሚኖሩባቸው እና የበርካታ ዲፕሎማቶች መቀመጫ የሆኑ ከተሞች ደግሞ ሰፋፊ እና ደረጃቸውን የጠበቁ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ከሌሏቸው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ሊሆኑ እንደማይችሉ ተመላክቷል፡፡
የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ነዋሪዎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባሻገር የመዲናዋን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማሳለጥና ሁለንተናዊና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን እያጠናከረ ለመሄድ እየተከናወነ ያለው ስራ ተስፋ ሰጭ እርምጃና አህጉራዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነቷን በማጎልበት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን የሚያጠናክር ሆኖ መቀጠሉንም ከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ይህንን በመረዳት አዲስ አበባን የሚመጥኑ ሰፋፊ የመንገድ መሠረት ልማቶችን እና ግዙፍ ተሻጋሪ ፕሮጀክቶችን የገነባ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በጀመረው 2ኛው ዙር የኮሪደር ልማትም ዋነኛ ዓላማው መሀል ከተማ ላይ ያለውን ደረጃውን ያልጠበቀና ጥራቱ የተጓደለ መሰረተ ልማትና ደረጃቸውን ያልጠበቁ የመኖሪያ ቤቶችን በማሻሻል እንዲሁም በከተማዋ የሚስተዋለውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ በማቃለል የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ 24/7 ህዝቡን በባለቤትነት እያሳተፈ እየሰራ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡
“ይሁን እንጅ ከተማ አስተዳደሩ የከተማዋን ፈተናዎች ባሏት ፀጋዎቿ በማሻገር ሁለንተናዊ ብልፅግናዋን ለማረጋገጥ በሚጥርበት በዚህ ወቅት የኮሪደር ልማትን መነሻ በማድረግ የግል ፍላጎታቸውንና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚሯሯጡ አልጠፉም” ሲል ገልጿል፡፡
ከልማት የፍርስራሽ ግምት ለግል ጥቅማቸው ሊያውሉ የሞከሩ አመራሮችንም አስተዳደሩ በዘረጋው የህዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ በከተማው የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡
በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 በካዛንችስ የኮሪደር ልማት ላይ ባልተገባ አካሄድና መንግስትና ህዝብ የጣለባቸውን ሃላፊነት ወደ ጎን በመተው ከኮሪደር ልማት ፍርስራሽ ላይ ለግል ጥቅማቸው ሊያውሉ የነበሩ የወረዳ አመራሮችን በትናንትናው ዕለት በቁጥጥር ስር በማዋል አስተዳደሩ ሌብነትና ብልሹ አሰራር የልማት ዕንቅፋት እንዳይሆን ተገቢውን እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡
ከዚህ አንፃር በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 06 ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ራሄል ኃ/ኢየሱስ ጨምሮ የወረዳው ስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደበበ ጉልማ፣ የወረዳው የፋይናስ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታደለ ግዛቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ተጠርጣሪዎቹ የኮሪደር ልማትን መነሻ አድርገው የፍርስራሽ ግምት ለግል ጥቅም ለማዋል በመሞከር ላይ እያሉ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ከከተማ እስከ ክ/ከተማ የፀጥታ መዋቅሩን በመጠቀምና ክትትል በማድረግ ግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጓል። በዚህም መሠረት የወንጀል ማጣራት ሂደቱ በሚመለከተው አካል እየተካሄደ ይገኛል ነው የተባለው።
ህብረተሰቡ አሁንም ሌብነትና ብልሹ አሰራርን በማረም እና ጥቆማ በመስጠት የሚያደርገውን ጥቆማ አጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሳስቧል።
በቀጣይም የተጀመሩ ልማቶችን በማሳለጥ ሌብነት እና ብልሹ አሰራርን አጥብቆ ለመታገል የሚያደረገውን ትግል አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከተማ አስተዳደሩ አረጋግጧል።