የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የአምራች ኢንዱስትሪውን ተሳትፎ በማሳደግ ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መሰረት የጣለ ነው- የኢትዮጵያ ልማት ባንክ

You are currently viewing የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የአምራች ኢንዱስትሪውን ተሳትፎ በማሳደግ ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መሰረት የጣለ ነው- የኢትዮጵያ ልማት ባንክ
  • Post category:ቢዝነስ

AMN – ታኅሣሥ 14/2017 ዓ.ም

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተወዳዳሪ አምራች ኢንዱስትሪ በመፍጠር ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መሰረት የጣለ እንደሆነ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት እመቤት መለሰ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ ከሐምሌ 2016 ጀምሮ ጠንካራ፣ በግሉ ዘርፍ የሚመራ፣ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት እና ለሥራ ዕድል ፈጠራ መሠረት የሚሆን የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ገቢራዊ ማድረጓ ይታወቃል፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪዎች የመለዋወጫ ችግራቸው ተፈትቶ ወደ ምርት እንዲገቡ በማድረግ ከማሻሻያው በኋላ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ 816 ሚሊየን ዶላር ተኪ ምርቶችን ማምረት የቻለበትን አቅም ፈጥሯል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት እመቤት መለሰ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬ በገበያ እንዲወሰን ያስቻለ ነው፡፡

ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በፊት በነበረው አሰራር የውጭ ምንዛሪ አቅርቦቱ የግሉን ዘርፍ ያገለለ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በዚህም የግሉ አምራች ኢንዱስትሪ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ሕገ ወጥ መንገድን ከመፈፀም አልፎ ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ለመሰማራት ተገዷል ብለዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የግል አምራቹን ዘርፍ ተሳትፎ በማሳደግ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማምጣት የሚያስችል መልኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የግሉን ዘርፈ የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ በመመለስ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ ምርት በማቅረብ በገበያው ተወዳዳሪ አምራች ኢንዱስትሪ መፍጠር ያስቻለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ 99 በመቶ ብድር ለግሉ ዘርፍ የተሰጠ መሆኑን የገለጸት ፕሬዝዳንቷ፤ ልማት ባንክ የፖሊሲ ባንክ በመሆኑ በራሱ ተጨማሪ ገቢ የሚያገኝበትን አሰራር ገቢራዊ አድርገናል ብለዋል፡፡

ይሄውም የአምራች ኢንዱስትሪው ያገኘውን የውጭ ምንዛሪ በነፃነት በመጠቀም በሀገሪቱ ያለውን ሀብት ጥቅም ላይ ማዋል ያስችላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review