AMN – ታኅሣሥ 14/2017 ዓ.ም
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያወጣቸው ሕጎች የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡና ተፈጻሚ ይሆኑ ዘንድ የበለጠ ጥንቃቄ መደረግ እንደሚኖርበት የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስተባባሪ ኮሚቴ የምክር ቤቱን የ2017 በጀት የሩብ ዓመት አፈፃፀም ገምግሟል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ፣ ምክር ቤቱ በቋሚ ኮሚቴዎቹ እና በተለያዩ አደረጃጀቶች እየተከናወኑ ያሉት ስራዎች በአፈፃፀማቸው በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ የሚያወጣቸው ህጎች የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡና ተፈጻሚ ይሆኑ ዘንድ የበለጠ ጥንቃቄ መደረግ እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል በፀደቁት ሕጎችም ቢሆኑ መታረም ያለባቸው ጉዳዮች በድጋሚ መታየት እንደሚችሉ ነው አፈ ጉባኤው ያስረዱት፡፡
ረቂቅ ህጎች ወደ ምክር ቤቱ ከመጡ በኋላ ሂደቱን ጠብቀው በፍጥነት መውጣት እንዳለባቸውና በአሁኑ ጊዜ ምክር ቤቱ በዝርዝር እያያቸው የሚገኙ ረቂቅ ህጎችም በጥልቀት ከታዩ በኋላ እስከ ጥር 30/2017 ተጠናቀው ለውሳኔ ሀሳብ መቅረብ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡
የምክር ቤቱ ጽህፈት አደረጃጀት አዲስ በጸደቀው አዋጅ መሰረት በቅርቡ እንደሚከናወን፣ የመንግስት ልማት ድርጅቶች የሚገመገሙበትን ፎርማት ማዘጋጀት እንደሚገባ የሚሉ ሀሳቦችን አፈ ጉባኤው አንስተዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው ምክር ቤቱ በበጀት ዓመቱ በተሻለ ቅንጅት በመስራቱ በህግ አወጣጥ፣ በክትትልና ቁጥጥር፣ በህዝብ ውክልና እንዲሁም በፓርላማ ዲፕሎማሲ የተከናወኑት ተግባራት አበረታች ስለመሆናቸው አንስተዋል፡፡
ለምክር ቤቱ ስራዎች ሙያዊ ድጋፍ የሚሰጡ ልምድ ያላቸው እና ምክር ቤቱን በሚመጥን መልኩ የህግ ባለሙያችን ማግኘት ይቻል ዘንድ የተለያዩ ሙከራዎች እየተደረጉ ስለመሆኑም የተናግረዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት ምክር ቤቱ በአህጉራዊ እና ዓለማቀፋዊ መድረኮች ላይ በቀጣይ ሀገራችን የተሻለ ተሳትፎ ማድረግ እንደምትችልም አስረድተዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ 5 ሕጎች የፀደቁ ሲሆን 23 ረቂቅ ህጎች በሂደት ላይ መሆናቸው በሪፖርቱ ተገልጿል።
በአስፈፃሚ መስሪያ ቤቶች የቀረቡ 98 የዕቅድና የአፈፃፀም ሪፖርቶች ተገምግመው ግብረ መልስ የተሰጠ ሲሆን፣ የተሰጡ ግብረ መልሶች መተግበራቸው ክትትል እየተደረገ መሆኑም ተጠቁሟል።
ቋሚ ኮሚቴዎች በ13 ክልሎች ባደረጉት ክትትልና ቁጥጥር የልማት ሥራዎች፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች፣ በዩንቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ሂደቶች እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የመስክ ምልከታ አድርገዋል።
ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ የተለያዩ ሀገራት ኢምባሲዎችና በተለያዩ የውጪ ሀገራት፤ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ፣ በሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲሁም በንግድና ኢንቨስትመንት በዓለም አቀፍ መድረክ ልምድ በማካፈልና በመውሰድ የፓርላማ ዲፕሎማሲ ሥራ መሰራቱ በሪፖርቱ መቅረቡን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።