
AMN – ታኀሣሥ 15/2017 ዓ.ም
የኢፌዴሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ፍሪደም ፈንድ (Freedom Fund) ከተባለ አለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመተባበር ፍልሰትንና ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን በመከላከል ዙሪያ የመገናኛ ብዙሃንን ሚና ለማጎልበት የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት አካሂዷል።
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህገወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከልና የተመላሽ ዜጎች ክትትልና ድጋፍ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደረጀ ተግይበሉ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፣ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ዜጎች በየጊዜው በህገወጥ መንገድ ከሀገር ሲወጡ በድንበር ጠባቂዎችና ሌሎች የተደራጁ አካላት እጅ እየወደቁ ከፍተኛ ለሆነ የጤና፣ የስነ-ልቦና፣ የአካል ጉዳት፣ የወሲባዊ ጥቃት፣ ለሰውነት አካል መሰረቅ ብሎም ለሞት እየተጋለጡ ይገኛሉ።
ድርጊቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተና በዜጎች ላይም እየደረሰ ያለው ጉዳት እየከፋ መምጣቱ ሁኔታውን እጅግ አሳሳቢ ያደርገዋል ብለዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት የወንጀል ድርጊት መሆኑንና አስከፊነቱን ለህብረተሰቡ ለማስገንዘብ፣ ተጎጂ ለሆኑ ተመላሽ ዜጎችን ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ድጋፍ ለመስጠት እንዲሁም ፍልሰትን የተመለከተ ሀገራዊ መረጃ ለማደራጀት ሰፊ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የሚዲያ አካላት የመረጃ ምንጭ ከመሆናቸው ባለፈ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከል በሚደረገው ሂደት ውስጥ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱና ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የፍሪደም ፈንድ ኢትዮጵያ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ቁምነገር አዲሱ በበኩላቸው፣ ድርጅቱ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል፣ ደህንነቱ የተጠበቀ ፍልሰትን ለማበረታታት፣ ተመላሽ ዜጎችን ለመደገፍ ብሎም በፍልሰት ምክንያት ለቤት ሰራተኛነት የተዳረጉ ታዳጊ ህፃናትን ህይወት ለመታደግ የሚያግዙ ሰፋፊ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ መናገራቸውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።