AMN-ታህሣሥ 15/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እና የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ እና ዓለምአቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዲኤታ አሊ መሃመድ ኦማር ዛሬ በአዲስ አበባ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ላይ አምባደሳደር ምስጋኑ የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ህዝቦች የማይነጣጠል መፃኢ ዕድል ያላቸው መሆኑን በመግለፅ ፥ ሃገራቱ ተባብሮ መስራት ችግሮች ሲጋጥሙም ተቀራርቦ መፍትሄ መሻት ይገባቸዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለአንካራው ስምምነት ተግባራዊ መሆን ቁርጠኛ ናት ያሉት አምባሳደር ምስጋኑ የሁለቱ ሃገራት ትብብር ማደግ ለቀጠናው ሰላም እና እድገት ወሳኝ እንደሆነም አመልክተዋል።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና ዓለምአቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዲኤታ አሊ መሃመድ ኦማር በበኩላቸው ሶማሊያ የአንካራው ስምምነት በተፋጠነ ሁኔታ እንዲተገበር ትሻለች ሲሉ ገልፀዋል።
ዛሬ በአዲስ አበባ መገኘታቸውም ለስምምነቱ ተፈፃሚነት ሀገራቸው ያላትን ዝግጁነት እንደሚያሳይ የጠቀሱት አሊ ኦማር ፥ ለሰላም መረጋገጥ እና ለጋራ እድገት የሶማሊያ መንግሰት ከኢትዮጵያ ጋር ተባብሮ በትብብር ይሰራል ብለዋል።
በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ባተኮረው የሚኒስትር ዲኤታዎቹ ውይይት ላይ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም መረጋገጥ ከፍተኛ መስዋዕትነትን እንደከፈለች አምባሳደር ምስጋኑ አስታውሰዋል።
ሁለቱ አካላት ለግንኙነታቸው መሻሻል አሁን የጀመሩትን ውይይት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ እንዲሁም በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ተቀራርበው እንደሚሰሩ ከውይይቱ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ማስታወቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡