AMN – ታኅሣሥ 15/2017 ዓ.ም
የኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር ትራንስፖርት እንቅስቃሴ የፀጥታ ሁኔታ ለማጠናከር የሚያስችል የባለድርሻ አካላት ውይይት በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት ተካሂዷል።
የውይይቱ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያና በጅቡቲ መካከል ሰዎችን በማመላለስ እና የሀገራችንን የገቢ እና ወጪ ምርትና ሸቀጦችን በማጓጓዝ ለኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ያለውን የኢቶዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር መሥመር ላይ አልፎ አልፎ በመሠረተ ልማት ላይ ከሚፈፀም ወንጀል ነፃ ለማድረግና ከሌሎች የወንጀል ስጋቶች ለማፅደት እንደሆነ ታውቋል።
ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ከኢቶዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር እና ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች የኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር ትራንስፖርት እንቅስቃሴ የፀጥታ ሁኔታ ላይ ሰፊ ውይይት ያደረጉ ሲሆን በፀጥታው ዙሪያ ያሉ ችግሮችን በጥናት ለመለየት አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
የባለድርሻ አካላቱ በቀጣይም የክልል የፀጥታ አካላትንና የክልል መስተዳደር አካላትን በጉዳዩ ላይ በማወያየት የአካባቢው ኅብረተሰብ ግንዛቤ በማሳደግ በባቡር ትራንስፖርቱ መስመር ላይ እየተፈፀሙ ያሉትን ውስን የፀጥታ ችግሮችን ለመቅረፍ በቁጠኝነት እና በተነሳሽነት ለመስራት መስማማታቸው ከፊደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ጋር ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙ ይታወሳል።