AMN-ታህሣሥ 16/2017 ዓ.ም
የገበያ ማረጋጋት ፣ ገቢ መሰብሰብ ፣ ሕገ-ወጥ ንግድ ቁጥጥርና ኢትዮጵያ ታምርት አብይ ግብረ-ሀይል የህግ ማስከበርና ቁጥጥር ንዑስ ኮሚቴ ውይይት አካሄዷል።
ግብረኃይሉ ባቀረበው ሪፖርት 936 አዋኪ ንግድ ድርጅቶች ፣ ያለ ንግድ ፈቃድ ሲነግዱ የተገኙ 1287 ንግድ ድርጅቶች እንዲሁም ባልታደሰ ንግድ ፈቃድ ሲነግዱ የተገኙ 249 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልጿል።
በመጋዘን የምግብ ፍጆታ በማከማቸት የተገኙ 5 ንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወስዷልም ተብሏል።
አጎራባች ከሆነው ሸገር ከተማ ጋር ህገ ወጥነትን በጋራ ከመከላከል እና ከመቆጣጠር አኳያ ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውም በውይይት መድረኩ ተገልጿል።
በትምህርት ቤቶች ዙሪያ ያሉ አዋኪ ድርጊቶችን ከመከላከል ረገድ በጋራ በመሰራቱ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውም ተነግሯል።

በትምህርት ቤቶች ዙሪያ ያሉ አዋኪ ድርጊቶች ላይ የተሰማሩ ተቋማት የዘርፍ ለውጥ እስኪያደርጉ ምንም አይነት አገልግሎት እንዳይሰጡ የውሳኔ ሀሳብ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
አዋኪ ድርጊቶችን በመከላከል እና በመቆጣጠር ረገድ የጋራ እና ተመሳሳይ አሰራር በተቋማት መካከል መዘርጋት እንደሚገባም የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ፣ ገበያው የተረጋጋ እንዲሆን እና የአቅርቦት እጥረት እንዳይገጥም በማድረግ በኩል ግብረ ሀይሉ ከፍተኛ አበርክቶ ማድረጉን ገልጸዋል።
በመርካቶ የተጀመረው ውጤታማ የደረሰኝ ግብይት ስርዓት በሌሎች የከተማዋ ክፍለ ከተሞች ላይ ተግባራዊ መደረግ እንደሚገባው ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ የሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ እና የህግ የበላይነትና ቁጥጥር ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ ፣ ከማህበረሰቡ በሚቀርቡ ጥቆማዎች መሰረት ሕገ ወጥ ንግድን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ስኬት መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
ሕግና ስርዓትን ተከትሎ የሚሰራ የንግድ ማህበረሰብ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት መላው ሕዝብ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ተጠይቋል፡፡
በዳንኤል መላኩ