AMN-ታህሣሥ 16/2017 ዓ.ም
ባለፉት ሶስት ዓመታት 9 ነጥብ 8 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች እውቀትን መሰረት ያደረገ ቋሚ የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ባለፉት ሶስት ዓመታት መንግስት የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት ለማሳለጥ ብሎም የሀገሪቷን ልማት ለማፋጠን የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
ብቁ የሰው ሀይልን በማፍራት ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ የሚያደርጉ ፖሊሲዎች፣ አዋጅ እና የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት ተግባራዊ ማድረጉን ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩም በእነዚህ ዓመታት በክህሎት የዳበረ አምራች ዜጋን የመፍጠር እና የስራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
እንደ ሀገር ዜጎችን ከክህሎት አኳያ ማብቃት እና የስራ እድል መፍጠር ብቻ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ተወዳዳሪነት የማያረጋግጥ በመሆኑ የአሰሪና ሰራተኛ ግኑኑኝነትን ሰላማዊ ማድረግ ላይም መሰራቱን ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ብቁ እና ሙያ ያለው ዜጋን ለማፍራት የዘርፉን አሰራርና ተቋማቶችን የስልጠና አሰጣጥ ስርዓቶችን ማዘመን የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።
ለላፉት ሶስት ዓመታትም አጫጭር የክህሎት ልማት ተግባራት ተጠናክረው የቀጠሉበት መሆኑን ተናግረዋል።
በባለፉት ሶስት ዓመታት ዘጠኝ ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች አጫጭር ስልጠናዎች በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስርዓት እንዲያልፉ መደረጉን አብራርተዋል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት 9 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች እውቀትን መሰረት ያደረገ ዘላቂ የስራ እድል መፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ሚኒስትሯ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ የገበያ መረጃ ስርዓት ቴክኖሎጂ ዘርፉን ሙሉ በሙሉ በማዘመን የመረጃውን ተአማኒነት እንደሚያሳድገው አክለዋል።
ኢትዮጵያዊያን የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት ለማፋጠን ስራ ጠባቂ ከመሆን ይልቅ ስራን በራስ መፍጠር የሚያስችላቸውን አቅም ሊያጎለብቱ እንደሚገባም ገልጸዋል።