AMN-ታህሳስ 18/2017 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሆለታ ባለ 500 ኪሎ ቮልት የማከፋፈያ ጣቢያ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመነጨውን ኃይል በአግባቡ እያከፋፈለ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የጣቢያው ኃላፊ አቶ ጥላሁን አዘዘው እንደገለጹት፣ የማከፋፈያ ጣቢያው እያንዳንዳቸው 750 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ያላቸው ሰባት ትራንስፎርመሮች አሉት፡፡
ጣቢያው በአሁኑ ወቅት ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአራት ተርባይን እየመነጨ ያለውን 1500 ሜጋ ዋት ኃይል ከዴዴሳ ማከፋፈያ ጣቢያ ተቀብሎ ወደ ተለያዩ ማከፋፈያ ጣቢያዎች እያሰራጨና ከግሪዱ ጋር እንደሚያገናኝ ገልጸዋል፡፡
ጣቢያው ከደዴሳ በባለ 500 ኪሎ ቮልት አራት መስመሮች ኃይል ተቀብሎ በ400 ኪሎ ቮልት በጥምር መስመር ለሱሉሉታ፣ ለሰበታና ለገላን ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኃይል እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ማከፋፈያ ጣቢያው በሦስት ባለ 33 ኪሎ ቮልት እና በስድስት ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች ለተለያዩ አካባቢዎች ኃይል እያቀረበ የሚገኝ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በባለ 132 ኪሎ ቮልት መስመር ደግሞ ለሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ ኃይል እየሰጠ ነው ብለዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቀሪ ተርባይኖች ወደ ሥራ ሲገቡ የመነጨውን ኃይል በሙሉ ተቀብሎ በአግባቡ ለማከፋፈል ዝግጁ መሆኑንም አቶ ጥላሁን ገለጸዋል፡፡
ጣቢያው ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂዎች መገንባቱን የጠቆሙት ኃላፊው ይህም የጣቢያው ደህንነት ለመጠበቅ፣ መስመሩ ላይ የሚኖረውን የኃይል መዋዥቅ ለመቋቋም እና የእቃ ብልሽቶች ሲያጋጥሙ ኃይል ሳይቋረጥ ችግሩን ለማስተካከል እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
ጣቢያው የአገር ውስጡን ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር ለውጭ አገራት ኃይል ለማቅረብ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የጠቆሙት አቶ ጥላሁን ብሔራዊ የኃይል ቋትን በማረጋጋት በኩል ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን ታሳቢ ያደረጉ የጥገናና የኦፕሬሽን ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ተርባይኖች 5 ሺ 150 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም እንደሚኖረው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።