AMN- መስከረም 7/2017 ዓ.ም
ለሽግግር ፍትሕ የተሟላ ትግበራና ፍትህን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት መገናኛ ብዙሃን የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሀን (ዶ/ር) ገለጹ።
በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲና በማስተግበሪያ ፍኖተ ካርታ ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃን አመራሮችና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በአዲስ አበባ እየተሰጠ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሀን (ዶ/ር) ፤ የሽግግር ፍትሕ የተሟላ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
የሽግግር ፍትሕ የተበደሉ ዜጎች የሚካሱባት፣ ሰላም፣ መረጋጋት፣ እርቅና የሕግ የበላይነት የሰፈነባት ሀገር ለመገንባትም መሰረት የሚያኖር መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የተፈጠሩ ችግሮችን በእርቅ፣ በካሳ፣ በይቅርታና የተጠያቂነት መርህ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን አንስተው፤ ለዚህም የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ የፖሊሲ ዝግጅት ስራው መጠናቀቁን አስታውሰዋል።
የሽግግር ፖሊሲ ዝግጅት ስራው መጠናቀቁን ተከትሎም የፖሊሲ መተግበሪያ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
በመሆኑም በዚህ የአሰራር ሂደት በደሎችን በማከም ሠላምና ዴሞክራሲ የሰፈነባት ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የህዝብ የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የህዝብ ተሳትፎ በሚፈለገው ልክ እንዲሆን ደግሞ የመገናኛ ብዙሃን የማስተማርና የማስገንዘብ ኃላፊነት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
ለሽግግር ፍትሕ የተሟላ ትግበራና ፍትህን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት መገናኛ ብዙሃን የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል።
በዚህ የአሰራር ሂደት በደልና ቁርሾዎችን በመፍታት የተሻለ ነገን የሚፈጥር ማህበረሰብ መገንባት ይገባል ሲሉም ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡