ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገር እናስረክባለን፡- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገር እናስረክባለን፡- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – ታህሳስ 29/2017 ዓ.ም

ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገር እናስረክባለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባ አዳነች ይህን ያሉት በሁለተኛው የኮሪደር ልማት እየተሳተፉ ለሚገኙ ሰራተኞችና አመራሮች የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ ባደረጉት የምሳ ግብዣ ላይ ነው፡፡

እናንተ የሀገር ባለውለታዎች ናችሁ፣እየገነባችሁት ያለው ፕሮጀክት ሳይሆን ሀገር ነው፤በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝቅ ያደረገንን ድህነት በስራ እየተዋጋችሁ ኢትዮጵያ እንድትበለፅግ መሰረት እየጣላችሁ ነው ብለዋል፡፡

ዛሬ እናንተ የጣላችሁት መሰረትም ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል፤ ትውልዱም እኛ ባለፍንበት መንገድ አያልፍም፤የተሻለ ሀገር እናስረክባለን ብለዋል ከንቲባ አዳነች፡፡

እኛ ትናንት የተረክብናቸውን በርካታ እዳዎች ዛሬ ለማስተካከል ጥረት እያደረግን እንገኛለን ያሉት ከንቲባ አዳነች ለሚቀጥለው ትውልድ ግን ምንዳን፣ተወዳዳሪ የሆነች፣ ልጆቿ ሁሉ የሚኮሩባት እና የሚደሰቱባትን ሀገር ለማስረከብ እየተጋን ነው ብለዋል፡፡

ይህን ዓላማ ለማሳካትም እናንተ ያለ ምንም እንቅልፍ ሌትና ቀን 24/7 እየሰራችሁ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች ይህም ስራ ባህል ወደ መሆን እየተሸጋገረ ያለበትን ስርዓት እየተገበራችሁ በመሆናችሁ ምስጋና ይገባችኋል ብለዋል፡፡

በኮሪደር ልማት ስራው ለብዙዎች የስራ እድል ተፈጥሯል ያሉት ከንቲባ አዳነች በዚህ ስራ ገቢያችን ያድጋል፣ የቱሪዝም መስህቦችም ይጨምራሉ፣ ይህም ለብልፅግና መረጋገጥ የበኩሉን ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

አሁን እየሰራችሁት ካለው ስራ የበለጠ ስራ ለመስራት እንደምትተጉ እርግጠና ነኝ ያሉት ከንቲባዋ፣ የማይቋረጥና ዘላቂ ልማትን የማረጋገጥ ተግባራችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች በኮሪደር ልማት ስራው እየተሳተፉ ለሚገኙ አመራሮች’ሰራተኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን አመስግነዋል፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review