AMN – ጥር 2/2017 ዓ.ም
ለታላቁ ህዳሴ ግድብ እዚህ ደረጃ መድረስ መላው ኢትዮጵያዊ በፐብሊክ ዲፕሎማሲ፣ በሞራል፣ በገንዘብ፣ በጉልበትና በዕውቀት ያደረገው ርብርብ በታሪክ ማህደር ትልቅ ስፍራ የሚይዝ ነው ሲሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ‹‹በህብረት ችለናል!›› በሚል መሪ ቃል የህዳሴ ግድብ ግንባታ ቦንድ ሽያጭና የሃብት ማሰባሰቢያ መርሀግብር አካሂዷል፡፡
የመርሃ-ግብሩ ላይ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት አስራ አራት ዓመታት ያለምንም የውጭ ዕርዳታም ሆነ ብድር፣ በራስ አቅም፣ ህዝባችንን በማስተባበር የወል ታሪካችን የሆነውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ በአባይ ወንዝ ላይ በመገንባት ወደ ፍጻሜው በመቃረባችን ኩራትና ደስታ ይሰማናል ብለዋል፡፡
ለዚህም በተለያየ መልክ ድጋፍ ላደረጋችሁ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ለግድቡ እዚህ ደረጃ መድረስ መላው ኢትዮጵያዊ በፐብሊክ ዲፕሎማሲ፣ በሞራል፣ በገንዘብ፣ በጉልበትና በዕውቀት ያደረገው ርብርብ በታሪክ ማህደር ትልቅ ስፍራ የሚይዝ ነው ብለዋል፡፡
ግድቡ አንድነትን፣ ፅናትን፣ የኢኮኖሚ ነፃነትን እና በራስ መቆም መቻልን የገነባንበትና የተማርንበት ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ በበኩላቸው የሀገራችን የፋይናንስ ተቋማት ከመንግስት እና ከህዝባቸው ጎን በመቆም ለዚህ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸው የዚህ ታሪክ አካል መሆናቸውን በተግባር ያረጋገጡበት ነው ብለዋል፡፡
የግድቡ የግንባታ ከ97 በመቶ በላይ መድረሱን አውስተው ከህዝቡ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ መሰብሰቡን ጠቁመዋል፡፡
አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ በተፋሰስ ልማት ከ120 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የጉልበት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን፤ በዲፕሎማሲው ረገድም ሀገራችን ከሶስትዮሽ ድርድሩም ባሻገር በዓለም አቀፍ መድረኮች ጭምር በመሟገት እና የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ስምምነት በመምራትና በተፈጥሮ ሃብቷ የመጠቀም ሉዓላዊ መብቷን ማስከበር በተግባር አረጋግጣለች ብለዋል፡፡
ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓ.ም.በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን ከላላ ከተማ በተደረገው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሃብት ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በታዳጊ ህፃን ሠሚራ እብራሂም አደም ለህዳሴ ዋንጫ ተንከባክባ ያሳደገችውን አውራ ዶሮ መስጠቷ ተመልክቷል፡፡
እዛው የሃብት አሰባሰብ ፕሮግራሙ ላይ የሰባት ዓመት ታዳጊዋ ያበረከተችው አውራ ዶሮ ለጨረታ ቀርቦ 17 ሺ ብር ተሸጦ ለግድቡ ግንባታ የ17 ሺ ብር ቦንድ እንደተገዛበትም ተጠቁሟል፡፡
በዛሬው መርሃ ግብር ላይ በሰባት አመቷ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ቦንድ በመግዛት ለሌሎች ምሳሌ የሆነችው የሰሚራ አስተዋፅኦ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት እውቅና በመስጠት ታዳጊዋን ህጻን እና እናቷን ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
በመርህግበሩ ላይ የተሳተፉ ባለሃብቶች፣ የባንክና የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶች ተወካዮች፣ ለግድቡ ድጋፍ አድርገዋል።
ብሔራዊ ባንክ 5 ሚሊዮን፤ ጋሻ ማይክሮ ፋይናንስ 30 ሺ ብር፤ አፍሪካ ቪሌጅ ማይክሮ ፋይናንስ 100 ሺ ብር፤ ወ/ሮ ወጋዳሁ አስራት በግል 100 ሺ ብር በቼክ፤ ልዩ ማይክሮ ፋይናስ ኢንስቲትዩት 100 ሺ ብር በቼክ፤ አንበሳ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማህበር 7 ሚሊዮን ብር፤ ንብ ኢንሹራንስ 13 ሚሊዮን የቦንድ ግዥ አድርገዋል፡፡
በድምሩ በመርሃ-ግብሩ ላይ ብቻ ሃያአምስት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሺ ብር የቦንድ ግዥ ተደርጓል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና እናት ባንክ በሚቀጥሉት ሳምንት ከቦርድ ውሳኔ በኋላ እንደሚያሳውቁ ቃል መግባታቸውን ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል ፡፡