• ማዕከሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከናወኑ ትልልቅ ጉባኤዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ያግዛል
በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1950ዎቹ መጨረሻ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከተመሰረተ በኋላ ዋና ፅህፈት ቤቱ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሆን ሲወሰን በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን ለማስተናገድ የሚመጥን የመሰብሰቢያ አዳራሽ አለመኖሩ ትልቅ ፈተና ነበር፡፡ የያኔው የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም ለድርጅቱ ጽህፈት ቤትና ለስብሰባ አገልግሎት የሚውል ህንጻ በአጭር ጊዜ እንዲገነባ አዝዘው፤ በአንድ ዓመት ከስድስት ወር፣ ይህንን አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ህንጻ ተገንብቶ እ.ኤ.አ. በ1961 በይፋ እንደተመረቀ የተባበሩት መንግስታት አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ይፋዊ ገፀ ድር ላይ “የአፍሪካ አዳራሽ አዲስ አበባ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ሰነድ ያሳያል፡፡
በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ውስጥ የሚገኘው የአፍሪካ አዳራሽ ከምርቃት በኋላ የተለያዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎችና ጉባኤዎችን አስተናግዷል።
በፈረንጆቹ አቆጣጠር 1963 በአፍሪካ ታሪክ ልዩ ቦታ የሚሰጠው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት ሲመሰረት በጊዜው ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡ 32 የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የድርጅቱን መመስረቻ ስምምነት (ቻርተር) የፈረሙበት ስፍራ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ከዚህ በኋላ አዲስ አበባ በተለያዩ ጊዜያት የአፍሪካ ህብረት ህንፃን ጨምሮ ትላልቅ ጉባኤዎችን ማስተናገድ የሚያስችሉ አዳራሾችና መሰረተ ልማቶች ያላቸው ደረጃውን የጠበቁ ዘመናዊ ሆቴሎች፣ የመሰብሰቢያና የኤግዚቢሽን ማዕከላት ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ አዲስ አበባ የኢትዮጵያውያን መሰባሰቢያ፣ የአፍሪካ ህብረት ዋና ፅህፈት ቤት መቀመጫ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሶስተኛ የዲፕሎማሲ ማዕከል እንደመሆኗ በዚህ ረገድ ያሏት መሰረተ ልማቶች ድርብርብ ሚናዋን ለመወጣት የሚመጥኑ እንዳልነበሩ ተደጋግሞ ሲነገር ይሰማል፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት አዲስ አበባን ልክ እንደ ስሟ “ውብና አበባ”፣ ለኑሮ ምቹና ሚናዋን በአግባቡ እንድትወጣ የሚያስችሉ በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። የወዳጅነት አደባባይ፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
ከሰሞኑ ደግሞ በኮሪደር ልማቱ በተዋበውና ልዩ ገፅታን በተላበሰው ሲኤምሲ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ሌላ ለከተማዋ ድምቀትን የጨመረ ፕሮጀክት እውን ሆኗል፡፡ በ40 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው፣ በዓይነቱ ልዩና ግዙፍ የሆነው የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ተገንብቶ ለህዝብ ክፍት ሆኗል፡፡
ማዕከሉ በውስጡ ከ3 ሺህ እስከ 4 ሺህ ሰዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው ሁለት ትላልቅ እና አስር ሺህ ሰዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው 8 አነስተኛና መካከለኛ የመሰብሰቢያ አዳራሾች አሉት። በተጨማሪም አንድ ሺህ አልጋዎች ያሏቸው ሁለት ትላልቅ ሆቴሎች፣ ሁለት የመገበያያ ሞሎችን ይዟል፡፡ ከአዳራሽ ውጪ 50 ሺህ ሰዎችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችል የኤግዚቢሽን ስፍራ፣ ሁለት አንፊ ቴአትር፣ ስፖርት መስሪያ፣ ባንክ፣ ኢንሹራንስ፣ የህክምና ተቋማት፣ ካፌና ሬስቶራንትን ጨምሮ በርካታ አገልግሎቶችን አሟልቶ የያዘ ነው፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የካቲት 22 ቀን 2017 ዓ.ም ማዕከሉን መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት፤ “በዚህ ኮንቬንሽን ማዕከል ንግድ እንነግድበታለን፤ ዲፕሎማሲ እንሰራበታለን፡፡ አፍሪካን የሚያገናኙ ዋና ዋና ኡደቶች እዚህ ቦታ ይከናወናሉ፡፡” ሲሉ የኮንቬንሽኑን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፣ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የተሰሩ በርካታ ስራዎች “አዲስ አበባን እንደ ስሟ አበባ፣ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን እያጠናከሩት፣ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ያለባትን ድርብርብ ኃላፊነት በብቃት የምትወጣና ተወዳዳሪ ከተማ” እያደረጓት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል የማያቋርጥ ሀብት መፍጠሪያ፣ ለገፅታ ግንባታና ለቱሪስት ስበት ትልቅ ሚና የሚጫወት ማዕከል ነው፡፡ ዓለም አቀፋዊ ኮንፈረንሶችን፣ የንግድ ውይይትና ስምምነቶችን፣ ባህላዊ መድረኮችን፣ ልዩ ኤግዚቢሽን የሚስተናገዱበት ቦታ ይሆናል፡፡ “አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤዎችን ብቻ አይደለም ማንኛውም ዓለም አቀፍ የሆኑ ጉባኤ፣ ኮንፈረንስ፣ ኤግዚቢሽን ለማስተናገድ የሚያስችላትን ግብአት እያሟላች የመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው፡፡” ብለዋል
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመሆን ኮንፈረንሶችን ለማዘጋጀት በሚሰራበት ጊዜ ትልቁ ፈተና የነበረው (እንደ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ያሉ) የተደራጁ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ያላቸው ስፍራዎች አለመኖራቸው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ ኮንፈረንሶች በተለያየ ሀገራት ይካሄዱ ነበር፡፡ የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ትላልቅ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ኮንፈረንሶችን በተሟላ ሁኔታ ለማዘጋጀት የሚያስችል በመሆኑ ጠቀሜታው የላቀ እንደሆነ በሚኒስቴሩ የመንግስት ኮንፈረንስ ዝግጅትና ፕሮቶኮል ዳይሬክተር አቶ እሸቱ ለገሰ ከሁለት ወር በፊት ማዕከሉን በጎበኙበት ወቅት ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከሰጡት አስተያየት መረዳት ይቻላል፡፡
ይህንን ሀሳብ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ በተለያየ ኃላፊነት ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲው መስክ ያገለገሉት አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ይጋሩታል፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ የአፍሪካ ህብረት እና የተለያዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እና በዓለም “ሶስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል ናት” ስንል ዓለም አቀፍ ኹነቶችን ደረጃውን በጠበቀና በተሟላ መልኩ ማስተናገድ የሚያስችል መሰረተ ልማት ነበረን ለማለት አልነበረም፡፡

አምባሳደር ጥሩነህ እንደሚናገሩት፣ የአፍሪካ መሪዎች ከዚህ ቀደም የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ በሚመጡበት ጊዜ ከአፍሪካ አዳራሽ ውጪ የሚሰበሰቡበት ስፍራ አልነበረም፡፡ የጉባኤ ታዳሚዎች ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አንስቶ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ግቢ ውስጥ የሚገኘው የአፍሪካ አዳራሽ እስኪደርሱ ድረስ፣ ከመንገድ በግራና በቀኝ ያሉት ስፍራዎች በቆርቆሮ ይታጠሩ ነበር፡፡ ምክንያቱም በመንገዱ ላይ ለእይታ ምቹ ያልሆኑ ቆሻሻ ስፍራዎች ይታዩ ነበር፡፡
ያንን ገፅታዋን የሚያውቁ ሰዎች፣ አሁን አዲስ አበባ ፅዱና ውብ፣ ምቹ መሰረተ ልማት ተሟልቶላት ሲመለከቱ የነበራቸው አመለካከት ይቀየራል፡፡ በኮንቬንሽን ማዕከሉ የሚገኙ ደረጃቸውን የጠበቁ የስብሰባ አዳራሾች፣ ባለአምስት ኮከብ ሆቴልና ሌሎች አገልግሎቶች ተሟልተው መገኘታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ትላልቅ ስብሰባዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ይጋብዛል። ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ቱሪዝም የስበት ማዕከል ያደርጋታል። የኮንቬንሽን ማዕከሉ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችንና ኹነቶችን ማስተናገድ የሚያስችል አቅም እየፈጠረች መሆኑን ያሳያል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ስብሰባዎችን ለማካሄድ “የተሟላ መሰረተ ልማት፣ ጥሩ አየር አለ” የሚለውን በማንሳት በኢትዮጵያ እንዲደረጉ ይሰራሉ፡፡
የተለያዩ የሀገራት መሪዎች፣ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ባለሀብቶች ዓለም አቀፍ ኹነቶችን ለመታደም ሰብሰብ ብለው ወደ አዲስ አበባ መምጣት ሌላ ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳ እንዳለው አምባሳደር ጥሩነህ ያስረዳሉ፡፡ ለስብሰባ የመጡ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች በአንድ ጊዜና በአንድ ቦታ በማግኘት ከኢትዮጵያ ጋር በተናጠል በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ባህል መስኮች ውይይትና ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ለምሳሌ፡- የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ በሚደረግበት ጊዜ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በጎን ከሌሎች ሀገራት መሪዎች ጋር የሚነጋገሩበት ሁኔታ አለ። ሚኒስትሮችም በደረጃቸው ጎን ለጎን ይወያያሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ሲወያዩ ድጋፏን የሚጠይቁ፤ ኢትዮጵያ ድጋፏን የምትጠይቃቸው ይኖራሉ፡፡
በቅርቡ በተካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ከአፍሪካ በተጨማሪ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች የታደሙበት ነበር፡፡ እንግዶቹ የኢትዮጵያ መልክና ገፅታ እየተለወጠ ሲመለከቱ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ የኢትዮጵያን ገጽታ ያስተዋውቃሉ፣ ሌሎች ስብሰባዎችም በኢትዮጵያ እንዲደረጉ ይሰራሉ። ለኢትዮጵያ ያላቸው አክብሮትና ተሰሚነቷ እያደገ ይሄዳል፡፡ ይህም ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ማህበራዊ ጥቅም እንደሚያስገኝ አንጋፋው ዲፕሎማት ያስረዳሉ፡፡

ማዕከሉን በአካል እንደጎበኙት የነገሩን አምባሳደር ጥሩነህ፣ ዓለም አቀፋዊ ኮንፈረንሶችን በተሟላ ሁኔታ ለማዘጋጀት ከማስቻሉም ባለፈ በውስጡ ለየት ያሉ ነገሮችን አካትቶ የያዘ መሆኑን ማየታቸውን ይናገራሉ። በማዕከሉ በሚገኙ አዳራሾች የሚገኙ ወንበሮች፣ ጠረጴዛዎችና የተለያዩ እቃዎች ኢትዮጵያን የሚገልፁ ናቸው። በተጨማሪም በቋሚነት በኢትዮጵያ የሚመረቱ ምርቶች፣ የባህል አልባሳት፣ ቁሳቁሶችና ሌሎች ኢትዮጵያን ሊገልፁ የሚችሉ ነገሮች በኤግዚቢሽን የሚታዩ በመሆኑ አንድ ከውጭ የመጣ ጎብኚ ኢትዮጵያን በተሻለ ለማወቅ የተለያዩ ቦታዎች መንቀሳቀስ ሳያስፈልገው በማዕከሉ ሁሉንም በአንድ ላይ የሚያገኝበት ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
በዓለም ላይ ውይይቶችን የማካሄጃ፣ በኢንቨስትመንት ዙሪያ የመመካከሪያ፣ እቃዎችን መግዣ፣ የመዝናኛ አገልግሎት የሚሰጡ የኮንቬንሽን ማዕከሎች በብዛት አይገኙም፡፡ ይህ ማዕከል ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ እንግዶች ከኢትዮጵያ ጋር በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በባህልና ሌሎች መስኮች ውይይት በማድረግ ግንኙነትን ለማጠናከር እንደሚያግዝ አምባሳደር ጥሩነህ ያነሳሉ፡፡
ከዚህም ባሻገር ማዕከሉ የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎችንና ኹነቶችን በማዘጋጀት ከፍተኛ ገቢ ማግኘት ያስችላል፡፡ በሚዘጋጁ ኤግዚቢሽኖች ሀገሪቱ ያላትን አቅም የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሀብቶች እንዲረዱ፣
እንዲወያዩ፣ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈስሱ ይረዳል፡፡ የንግድ ልውውጥ እንዲጠናከር፣ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ለመፍጠር እየተሰራ በመሆኑ ይህንን ለመጠቀም አፍሪካውያን ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ከኢትዮጵያ ምን መግዛት እንችላለን? የሚለውን በቀጥታ ማየት፣ ከአምራቾች ጋር መገናኘትና መወያየት ይችላሉ፡፡ የሀገር በኢኮኖሚ ማደግና መበልፀግ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ፣ ሀገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ወዳጆች ማፍራት፣ ያላትን ክብርና ተሰሚነቷን ከፍ እንደሚያደርግ አንጋፋው ዲፕሎማት አስረድተዋል፡፡
በጥቅሉ የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ኩነቶችና ኮንቬንሽን ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪና ቀዳሚ እንድትሆን ከማገዙም ባለፈ በዲፕሎማሲው መስክ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን የሚያስገኝ ነው፡፡
በስንታየሁ ምትኩ