መርሃ ግብሩ ምን ያህል የጤናውን ዘርፍ እያገዘ ነው?

You are currently viewing መርሃ ግብሩ ምን ያህል የጤናውን ዘርፍ እያገዘ ነው?

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 እያዩ ገደል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩት ወይዘሮ ወይንሸት አለማየሁ የጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ማግኘት ከጀመሩ ከ6 ዓመታት በላይ ሆኗቸዋል። ባለሙያዎቹ የተለያዩ የምክር አገልግሎቶችን ይሰጧቸዋል፡፡ በተለይም አካባቢያቸውን በንጽህና በመያዝ ከንጽህና ጉድለት የሚመጡ ተላላፊ በሽታዎችን መከላከል የሚችሉበትን ትምህርት ደጋግመው ያስገነዝቧቸዋል፡፡ ይህን ማድረግ መቻላቸውም ቤተሰባቸው በተለይም የልጅ ልጆቻቸው በየጊዜው በጉንፋንና ተያያዥ ተላላፊ በሽታዎች እንዳይያዙ አድርጎላቸዋል፡፡ በጤና ኤክቴንሽን ባለሙያዎች በጤና አጠባበቅ ዙሪያ የምክር አገልግሎት ከማግኘታቸው በፊት ቶሎ ቶሎ ጤና ጣቢያ ይመላለሱ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ያለባቸውን የደም ግፊት እንዲቆጣጠሩ በደጃቸው ክትትል ያደርጉላቸዋል። በጤናቸው ላይ ለውጥ ሲመለከቱም አመጋገባቸውን እንዲያስተካክሉና ተገቢ ህክምና እንዲያገኙ ሙያዊ ምክር ይለግሷቸዋል፡፡ ቀደም ሲል ለደም ግፊት ህመማቸው ምን አይነት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ግንዛቤው አልነበራቸውም። ክትትልም፣ ቁጥጥርም አያደርጉም ነበር፡፡ አሁን ላይ ብዙ ጥቅም አግኝተዋል፡፡

ወይዘሮ የኔውብ ደመቀ ሌላዋ የጤና ኤክስቴንሽን ተጠቃሚ እናት ናቸው፡፡ እሳቸውም የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እየመጡ ጤናቸውን እንደሚከታተሉላቸውና የተለያዩ ትምህርቶችን እንደሚሰጧቸው ነግረውናል። ውሀውን እያፈሉ እንዲጠጡ፣ የአካባቢና የግል ንጽናቸውን እንዲጠብቁ ያስተምሯቸዋል፡፡ ከሚያገኙት ግንዛቤ በመነሳትም በአሁኑ ወቅት የቤታቸውንና የአካባቢያቸውን ንጽህና መጠበቅ ችለዋል፡፡ በዚህም በየጊዜው በጉንፋን ከመያዝ ድነዋል፡፡ ተላላፊ ከሆኑ እና ካልሆኑ በሽታዎችም እንዴት ራሳቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው በዋናነት አስቀድመው እንዴት መከላከል እንደሚችሉ በቂ ግንዛቤ አግኝተዋል፡፡ ይህም ደስተኛና ጤናማ ሆነው እንዲኖሩ እድል ፈጥሮላቸዋል፡፡

ወ/ሮ የኔውብ ደመቀ ከጐረቤታቸው ጋር በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ትምህርት ሲሰጣቸው

የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዋ ሲስተር መስቀሌ ገላሼ በበኩሏ ሥራዋን ወዳውና በፍቅር እንደምትሠራ ትናገራለች፡፡ “ጤና ተቋም ውስጥ ተቀምጦ ከመሥራት ቤት ለቤት ተንቀሳቅሶ መሥራት ከባድ ቢሆንም፤ ማህበረሰቡ በሚያገኘው አገልግሎት ሲደሰት ማየትና ምርቃታቸውን ማግኘት ድካምን በእጅጉ ያስቀራል” ስትል ለሥራዋ የሰጠችውን ዋጋ ትናገራለች፡፡

እንደ ሲስተር መስቀሌ ማብራሪያ፤ ሥራው የስነ ልቦና ደስታ ስላለው ብርታት ይሰጣል፡፡ ቤት ለቤት ስትሄድ ማህበረሰቡ የሚሰጣት ክብርና ፍቅር ልዩ ነው፡፡ የጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ጥቅሙን ህብረተሰቡ በሚገባ ተረድቶታል፡፡ ለሥራውም፣ ለሠራተኞቹም ጥሩ አክብሮት አለው። ሥራው አበረታች ውጤት ማምጣቱ በገሃድ እየታየ ነው፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ፤ በሥራ አጋጣሚ ያገኘናቸው አንዲት እናት በመኪና አደጋ ምክንያት የአልጋ ቁራኛ ሆነው ሲሰቃዩ ከቆዩ በኋላ፤ የጤና ኤክስቴንሽን ቡድኑ ባደረገላቸው ክትትልና ህክምና መዳን መቻላቸው ይጠቀሳል።  ይህንን መሰል ስኬት  የአገልጋይነት ስሜትና ፍላጎትን ይጨምራል በማለትም ከገጠመኟ ቀንጭባ ነግራናለች፡፡

 እ.ኤ.አ. በ2023 በላይቤሪያ በተካሄደው የአፍሪካ የጤና ኮንፈረንስ “ኢትዮጵያ መከላከልን መሰረት ያደረገውን የጤና ፖሊሲ በመተግበር ውጤት አምጥታለች” በሚል ሽልማት አግኝታለች። አህጉር አቀፍ ሽልማት እንድታገኝ ባስቻላት የጤና ኤክስቴንሽን መስክ፤ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እና የዘርፉ አመራሮች የበኩላቸውን አይተኬ ሚና ተጫውተዋል። ሙያቸውን ወደውና አክብረው ከሠሩና እየሠሩ ካሉት መካከል ሲስተር መስቀሌ ገላሼ የሽልማት መርሃ ግብር ላይ በአካል የመታደም ዕድልን አግኝታለች፡፡ ኢትዮጵያን ወክላም ለ54 የአፍሪካ ሀገሮች ተሞክሯቸውን እንዳካፈለች አጫውታናለች፡፡ በወቅቱም ኩራት እንደተሰማትና የበለጠ ስንቅና ትጥቅ እንደሆናትም ገልጻልናለች። “ማህበረሰቡን ከማገልገሌ በተጨማሪ ሀገሬን የሚያስጠራ ስራ በመስራቴ ደስተኛ ነኝ”  ስትልም ሲስተር መስቀሌ ተናግራለች፡፡

  ሲስተር ማርታ ሰጠ በተመሳሳይ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ናት፡፡ ለ6 ዓመታት ያህል ማህበረሰቡን አገልግላለች፡፡ “በእኔ ምክንያት አኗኗራቸውን የለወጡና ጤናማ የሆኑ የቤተሰብ አባላትን ሳይ ደስ ይለኛል፡፡ በተለይም ጤና ተቋም መሄድ ለማይችል ሰው አገልግሎት መስጠት ደስታው ድርብ ድርብርብ ነው” ትላለች ሲስተር ማርታ፡፡ ለምሳሌ በደም ግፊት ምክንያት ለረጅም ጊዜ አልጋ ላይ ውለው የነበሩ እናት በሷ ምክንያት ወደ ህክምና እንደሄዱ፣ ያቋረጡትን መድሀኒት እንደገና መውሰድ እንደጀመሩ፣ በዚህም ጤናቸው መሻሻል እንዳሳየና በታየው ውጤትም ክትትል የሚያደርግላቸው ሀኪም እንደተደሰተ በማሳያነት አንስታለች፡፡

ስራው አድካሚ ነው፤ ፈታኝነትም አለው። በተለያየ መልኩ የማይቀበል ሰው ያጋጥማል። ቤት ለቤት ሄዳ ማህበረሰቡን የምታገለግለው በመጀመሪያ ማን ምን ይፈልጋል የሚለውን ከለየች በኋላ እንደሆነ ነው የምትናገረው፡፡ በሳምንት አራት ቀን ቤት ለቤት ተንቀሳቅሰው የሚሰሩ ሲሆን የሳምንቱ መጨረሻ አርብ እቅድ የሚታቀድበት ነው። በየቀኑ ስድስት ህጻናትን፣ ሁለት የማይቋረጥ መድሀኒት የስኳር፣ የልብ፣ የአስም  ወዘተ መድሃኒት የሚወስዱ ግለሰቦችን ቤት እና ሁለት ደግሞ ሌሎች በሚል የተለያዩ ኬዝ (ከጤና ጋር በተያያዘ) ጉዳይ ያላቸውን ሰዎች እንደየጉዳያቸው አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡፡

በተጨማሪም በህመምና በእድሜ መግፋት ምክንያት አልጋ ላይ ቀርተው ሰውነታቸው የሚቆሳስሉ ሰዎችን የማከም ስራ ይሰራል። ነፍሰጡር እናቶች አስፈላጊውን ክትትል እንዲያደርጉ ትምህርት ይሰጣል። በእርግዝና የሚከሰቱ አደገኛ ምልክቶች፣ ለጽንሱም ሆነ ለራሷ ማድረግ ያለባትን ትምህርት እና ክትትል እንድታደርግ ይደረጋል። ለህጻናት ከመደበኛ ክትባት በተጨማሪ የሚሰጠውን ክትባት ይሰጣሉ፡፡ መደበኛ ክትባት አንድ ዓመት ከሶስት ወር ስለሚያበቃና እስከ አምስት ዓመት ድረስ የሚሰጠውን ክትባት እናቶች ስለሚዘነጉ ቤት ለቤት እና በየትምህርት ቤቱ ተንቀሳቅሳ እንደምትሰጥ ነው ሲስተር ማርታ የምትገልጸው፡፡

በእቅዷ በየቀኑ 10፣ በወር 160 አባዎራዎች ቤት የምትሄድ ቢሆንም፤ ከእቅዷ በላይ በርካታ አባዎራዎችን የምትጎበኝበት አጋጣሚ አለ፡፡ የተለያዩ አገልግሎቶችንም ትሰጣለች፡፡ በአንድ አባወራ ቤት ውስጥ የህጻን ክትባት እና የምክር አገልግሎት የሚያስፈልገው ህመም ያለበት ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ ነፍሰጡር እናት ካለች ቅድመ ወሊድ ትምህርት ወይንም ደግሞ ቤተሰብ እቅድ ትምህርት ይሰጣታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ፕሮግራሙ ከመከላከል በተጨማሪ ህክምናም እየተሰጠበት ነው፡፡ የተለያየ ሙያ ያላቸው ባለሙያዎች በቡድን ስለሚኬድ ቁስል ማጠብና ማከምም አለ። መድሀኒትም ይሰጣል። እንደአስፈላጊነቱ የላቦራቶሪ ምርመራም ይሰራል። ስለዚህ በአንድ አባዎራ ቤት ውስጥ በርካታ አገልግሎቶች ይሰጣሉ ስትል የሚሰጠው አገልግሎት ዘርፈ ብዙነት አብራርተዋል፡፡

በሽሮሜዳ ጤና ጣቢያ የሚመራው የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም አተገባበርና ውጤት ምን እንደሚመስል የጤና ጣቢያው የቤተሰብ ጤና ዲፓርትመንት ሀላፊ ሲስተር አስቴር ግርማ ሀሳባቸውን አጋርተውናል። በጤና ጣቢያው 7 የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የሚገኙ ሲሆን በ7 ቀጠናዎች ተንቀሳቅሰው ነው የሚሰሩት። እያንዳንዳቸው 500 አባዎራዎችን ተደራሽ ያደርጋሉ፡፡ ፕሮግራሙ ከተጀመረበት ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2009 ዓ.ም ድረስ መከላከልን መሰረት ያደረጉ 16 የጤና ፓኬጆችን ይተገብራሉ። በእያንዳንዱ አባዎራ ህጻናት፣ አረጋውያን፣ ነፍሰጡር ሴቶች ይገኛሉ። የእናቶችና ህጻናት ጤና፣ የአካባቢ ቆሻሻ አጠባበቅ፣ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች እንደ የስኳር ህመም፣ የደም ግፊት እና የመሳሰሉትን ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ይተገበር ነበር፡፡

ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ የጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎቱን በማሳደግና ህብረተሰቡ ተጨማሪ አገልግሎቶችን እንዲያገኝ ለማድረግ የተለያየ ሙያ ያለው ቡድን ተዋቅሮ በጋራ በመሆን ማህበረሰብ አቀፍ ጤና አጠባበቅ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ህክምና የሚሰጥ፣ አዋላጅ፣ ፋርማሲና የላብራቶሪ ባለሙያ ከጤና ኤክስቴንሽኗ ጋር አንድ ላይ በመሰማራት ለማህበረሰቡ አገልግሎት እየተሰጠ ነው፡፡ ይህም የጤና ጣቢያውን መጨናነቅ ከማስቀረቱም በላይ ጤና ጣቢያ መጥተው መታከም የማይችሉ አቅመ ደካሞችን ተደራሽ ለማድረግ ፋይዳው የላቀ ነው፡፡

እንደ ዲፓርትመንት ኃላፊዋ ገለጻ፣ የቤት ለቤት ህክምና መሰጠት መጀመሩ ብዙ ጥቅሞችን አስገኝቷል፡፡ አንደኛ እናቶቻቸው አስበው ወደ ጤና ጣቢያ የማያመጧቸውን ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትን የሆድ ውስጥ ህመም መከላከያ መድሀኒት፣ ቫይታሚን ኤ መድሀኒቶችን እንዲያገኙ አስችሏል፡፡ ሌላው የአልጋ ቁራኛ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ባሉበት ህክምና እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ በጽዳት ጉድለት ምክንያት የሚመጡ ተላላፊ በሽታዎችን መቀነስ ተችሏል። ከማህበረሰቡ አኗኗር ጋር በተያያዘ የሚመጡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን እንደ ግፊትና ስኳር ያሉ በሽታዎችን ለመከላከል ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ተሰርቷል። ፕሮግራሙ የሚተገበረው ከቤት ለቤት አገልግሎት በተጨማሪ በትምህርት ቤቶች፣ በስራ ቦታ እና በወጣት ማእከላት እንዲሁም ለጎዳና ተዳዳደሪ ነው፡፡

ሲስተር አስቴር አያይዘውም፤ የመረጃ አያያዛቸው የተደራጀ በመሆኑ በየእለቱ ምን እንደሰሩና እንዴት እንደሰሩ ያሳያል። እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል ምን አይነት ህመም እንዳለበት፣ ምን አይነት አገልግሎት እንደተሰጠው፣ የሚሰጡ አገልግሎቶች በፎቶ ግራፍ በተጨባጭ ሰንዶ በማስቀመጥ ረገድ አርአያነት ያለው ስራ ተሰርቷል። ክፍለ ከተማው በሰራው ሥራ ሞዴል ለመሆን ችሏል። በዚህም በ2015 ዓ.ም ከጤና ሚኒስቴር ዋንጫና ሰርተፍኬት ተሸልሟል፡፡ በአፍሪካ ደረጃም ላይቤሪያ ላይ እ.ኤ.አ በ2023 በተዘጋጀው የጤና ልማት ፕሮግራም በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ማህበረሰባዊ ለውጥ መጥቷል በሚል ኢትዮጵያን ወክለው አዋርድ እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡

በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አማካኝነት በተሰሩ ስራዎች ቅድመ መከላከልን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውን ከላይ የተጠቀሰው ተግባር አስረጂ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ተግባራት በእኩል እንዲሰፉ እና ከዚህም በላይ እንዲጠናከሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ 

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የጤና ማበልጸግ እና በሽታ መከላከል ዳሬክተር አቶ ጌቱ ቢሳን በከተማዋ መከላከልን መሰረት ያደረገው የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ምን ውጤት እንዳመጣ ጠይቀናቸዋል፡፡ አቶ ጌቱ በሰጡት ምላሽ፤ በአዲስ አበባ ከተማ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም የተጀመረው በ2002 ዓ.ም ነው፡፡ በፕሮግራሙ 1 ሺህ 200 የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሙን የተለያየ ሙያ ያላቸውን ባለሙያዎች በህብረተሰብ ጤና ቡድን በማደራጀት መከላከልን መሰረት ያደረገ የህብረተሰብ ጤና አገልግሎት በመስጠት የጤና አገልግሎቱን ተደራሽ የማድረግ ስራ እየተከናወነ ነው፡፡ በተቀናጀው የህብረተሰብ ጤና አገልግሎት ህብረተሰቡ የጤና አገልግሎት ቤት ለቤት እያገኘ ነው ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ጌቱ ገለጻ፤ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሙ የእያንዳንዱ ቤተሰብ መሰረታዊና ወቅታዊ የጤና መረጃ በሚፈለገው ልክ እንዲደራጅና እንዲታወቅ በማድረግ ቀጣይ ለሚሰጠው የጤና አገልግሎት ምቹ መደላድል ይፈጥራል፡፡ የህብረተሰቡ የቆሻሻ አወጋገድ ስርአት አድጓል ሲሉም አክለዋል፡፡

አቶ ጌቱ አያይዘውም፤ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ዋና አላማ ግንዛቤ መፍጠር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር እናቶች በጤና ተቋማትና በሰለጠነ ባለሙያ የመውለድ ምጣኔ ከ12 እስከ 15 በመቶ የነበረው የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም መተግበር ከጀመረ ወዲህ  ወደ 98 በመቶ አድጓል። ሌላው የክትባት ሽፋን 100 በመቶ ሆኗል። በዚህም የእናቶችና ህጻናት ሞት ቀንሷል፡፡ ማህበረሰቡ ባገኘው ግንዛቤ የግልና የአካባቢውን ጽዳት መጠበቅ መቻሉ የተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች እንዲቀንሱ አድርጓል። ተላላፊ በሽታዎች ቀነሱ ማለት ደግሞ የሰዎች የመኖር ምጣኔ ጨምሯል፤ ከነበረበት 45 በመቶ ወደ 65 በመቶ እየደረሰ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በለይላ መሃመድ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review