AMN – መስከረም 23/2017 ዓ.ም
ሙስና ወንጀል ብቻ ሳይሆን እጅግ አስነዋሪ እና አዋራጅ ተግባር ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በፌዴራል የሥነምግባር እና የፀረ ሙስና ኮሚሽን የተዘጋጀውን ብሔራዊ የሙስና ወንጀል መረጃ ጥቆማ መቀበያ የዲጂታል አሠራር ሥርዓትን አስጀምረዋል፡፡
ተግባራዊ የተደረገው ይህ የዲጂታል አሰራር፤ ሙስናን የሚጠየፍ ትውልድ ለመገንባት፤ ሙስና ወንጀል እንጂ ክብር አለመሆኑን ለማሳየትና ሙስናን ከአሠራር ሥርዓት ለማውጣት የሚያግዝ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡
የሙስና ድርጊት የተበላሸ አስተሳሰብ፣ የተበላሸ ባህል እና የተበላሸ አሠራር ውጤት ነውም ብለዋል፡፡
ይህንን የተበላሸ የአሠራር ሥርዓትን ለማስተካከል ደግሞ የተቋማትን የማስፈጸምና የመፈጸም ዐቅም የሚያጎለብት የዲጂታል አሠራር ሥርዓትን መዘርጋት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የሀገራችን ተቋማት ከሙስና እና ብልሹ አሠራር የጸዳ አገልግሎት በመስጠት የዜጎችን እርካታና አመኔታን በማሳደግ የተጀመረውን የብልፅግና ጉዞ ለማሳካት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
የፀረ ሙስና ተቋማትም ተግባርና ኃላፊነታቸውን በተቀላጠፈ መንገድ ለመፈፀም እንዲችሉ የለማውን አጋዥ የዲጂታል ሲስተም በታማኝነት እንዲጠቀሙበትም አሳስበዋል፡፡