ምክር ቤቱ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት የሚያግዝ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጸደቀ

You are currently viewing ምክር ቤቱ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት የሚያግዝ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጸደቀ

AMN – መጋቢት 4/2017 ዓ.ም

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ19ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ፣ የሂሳብ ባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት ፣ የሀገር ሃብትን ለመጠበቅና ኢኮኖሚን ለማፋጠን ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡

የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጀ ሪፖርት እና የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

ሰብሳቢው አያይዘውም ረቂቅ አዋጁ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎችን ለማፍራት፣ ጥራት ያለው የፋይናንስ ስርዓት ለመዘርጋት እንዲሁም የሀገርን ኢኮኖሚ ዕድገት ለማፋጠን አቅም የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የሂሳብ ባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ በዘርፉ እየተከሰቱ ያሉ የገንዘብ ብክነትን ለማስቀረት እና የህዝብና የሀገርን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ መሆኑን ሰብሳቢው አስገንዝበዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ መኮነን (ዶ/ር) በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ተሞክሮዎችን መሰረት ያደረገ መሆኑን ተቋመው፤ የፋይናንስ አቅምን ለማሳደግ እና ኢንቨንስትመንትን ለማሳለጥ ኢንስቲትዩቱ ሚናው የጎላ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

ሀገራችን ከፍተኛ ውጪ እያወጣች በጎረቤት ሀገራት ባለሙያዎች ታሠራ የነበረው የሂሳብ ስራን በሀገር ውጥ ባለሙያዎች ለመተካት አቅም ይፈጥራል ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡

በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ኢንቨስትመንት በማሳለጥ በሀገር ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ የሂሳብ ባለሙያችን በማፍራት በዘርፉ የሥራ ዕድል ጭምር ለመፍጠር ያግዛል ሲሉ የምክር ቤት አባላቱ ገልጸዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ተግባር ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተግባር እና ኃላፊነት ጋር ያለው ልዩነት እና አንድነት በግልጽ በአዋጁ መቀመጥ አለበት ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ፣ አዋጅ ቁጥር 1372/2017 አድርጎ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን ከምክር ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review