AMN-ጥር 1/2017 ዓ.ም
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የነዳጅ ውጤቶችን ግብይት ስርዓት ለመደንገግ የወጣውን ረቂቅ አዋጅ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ስብሰባው የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው የረቂቅ አዋጁ የውሳኔ ሀሳብ ላይ ሰፊ ውይይት አድርጓል።
የውሳኔ ሀሳቡን ያቀረቡት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አይሻ ያህያ፥ የነዳጅ ውጤቶች ካላቸው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ አንጻር ስትራቴጂክ ምርቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
አዋጁ የተዘጋጀውም የነዳጅ ውጤቶችን ስትራቴጂክ አቅርቦት፣ ክምችትና ስርጭት፣ ደህንነትና ጥራት ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆን ለማድረግ ነው ብለዋል።
የነዳጅ ውጤቶችን ከአስመጪ እስከ ተጠቃሚ ድረስ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ፣ ግልፅ፣ አስተማማኝ፣ ፍትሐዊ የአቅርቦት ስርጭት ለማድረግ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።
በዚህም በነዳጅ የግብይት ስርዓት ሰንሰለት ውስጥ እየታዩ ያሉ ህገወጥ ተግዳሮቶችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ነው ያነሱት።
በዘርፉ የተሰማሩ የነዳጅ ተቋማትና ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ ብቃት ላይ የሚገኙ መሆናቸውን በማረጋገጥ ደህንነቱ የተጠበቀና ህጋዊ የነዳጅ ውጤቶች ግብይት ለማስፈን ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የነዳጅ ውጤቶች ግብይት በሰውና በእንስሳት ጤና በንብረትና በአካባቢ ደህንነት ላይ ጉዳት በማያደርስ ሁኔታ መከናወኑን ለማረጋገጥ አስፈላጊ በመሆኑ አዋጁ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰጡት አስተያየት አስፈላጊና ጊዜውን የጠበቀ ነው ብለዋል።
ነዳጅ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚመጣ እንደመሆኑ ስርጭቱን በተገቢው ሁኔታ ለመቆጣጠርም አዋጁ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል።
ሆኖም ህገወጥ የነዳጅ ግብይቶችን በቆጣጠር ሂደት የመንግሥት ተቋማት ጠንካራ እርምጃ እንደማይወስዱ በማንሳት የአዋጁ ተግባራዊነት ላይ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ ለህገወጥ ግብይቱ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሚና ያላቸው የመንግሥት አካላት ቢኖሩ ምን ዓይነት እርምጃ እንደሚወሰድባቸው በአዋጁ አልተካተተም ብለዋል።
የነዳጅ ማደያዎች 24 ሰዓት በሲሲቲቪ ካሜራ እና በሌሎች ቴክኖሎጂዎች የታገዘ የአሰራር ስርዓት ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ቁጥጥር የሚደረግበት ሁኔታ ቢፈጠር ሲሉም ጠይቀዋል።
ነዳጅ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሰረታዊ ግብዓት በመሆኑ የአቅርቦት ችግሩ ላይ ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳህረላ አብዱላሂ በሰጡት ማብራሪያ፥ ህገወጥ የነዳጅ ምርቶች ላይ የሚሳተፉ አካላት ጠንካራ ቅጣት እንዲጣለባቸው የተፈለገው አስተማሪ እንዲሆን ነው ብለዋል።
የነዳጅ ስርጭት ሂደቱን በአግባቡ ለመቆጣጠርም በተሽከርካሪ ላይ ጂፒ ኤስ መገጠሙ መሻሻል ፈጥሯል ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፥ የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለት ስርዓት መዘርጋቱንም ተናግረዋል።
ከዚህም ባለፈ እያንዳንዱ ማደያ ምን ያህል ነዳጅ እንዳለው በየጊዜው ክትትል ማድረግ የሚያስችልና በሳተላይት መረጃ ጭምር መቆጣጠር የሚያስችል ቴክኖሎጂ መልማቱን አንስተዋል።
በአዋጁ ነዳጅን በታሪፍ ያለመሸጥ ችግሮችን ለማስተካከል፥ ድርጊቱን በሚፈጽሙ አካላት ላይ ቅጣት እንደሚጣል መደንገጉንም ገልጸዋል።
አዋጁ የሚቀርበው ነዳጅ በአግባቡ ለተጠቃሚዎች እንዲደርስና የግብይት ስርዓቱን ለማዘመን ታሳቢ ተደርጎ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ምክር ቤቱም የረቂቅ አዋጁን የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ በሁለት ተቃውሞ፣ በአንድ ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ማጽደቁን ኢዜአ ዘግቧል።