ታህሣሥ 4/2017 ዓ.ም
ዛሬ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የቃሊቲ ኢንዱስትሪ ዞን እና የልህቀት ማዕከልን መጎብኘታቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኀበራዊ ትስስር ገፃቸው ባጋሩት መልዕክት፣ ኮርፖሬሽኑ በተለያዩ ሀገራዊ ስትራቴጂክና ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽዖ ለማጠናከር የጀመረው ተቋማዊ ሪፎርም አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ የኮንስትራክሽን ግብዓት ማምረቻ ኢንዱስትሪ ዞን በመገንባት በተኪ ምርትና በውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ የጀመረው እንቅስቃሴ ለዘርፉ እመርታዊ ለውጥ ወሳኝ ነው ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ዞኑ የማምረት ዐቅሙን በማሳደግ የግንባታ ግብአቶችን እያመረተ መሆኑ በዘርፉ የሚያጋጥም የግብአት እጥረትን በእጅጉ ይቀርፋልም ነው ያሉት።
ኮርፖሬሽኑ የኢትዮጵያን የግንባታ ኢንዱስትሪ ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ተቋማዊና ሀገራዊ ሚናውን ማጠናከርና ዐቅሙን እንዲያጎለብት መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡