ስልክን ወደ ሙዚቃ መሣሪያነት የሚቀይር ቴክኖሎጂ ተፈለሰፈ

AMN-ኅዳር 13/2017 ዓ.ም

ስልክን ወደ ሙዚቃ መሣሪያነት የሚቀይር “ዜፊሮ” የተሰኘ (ዲጂታል የሙዚቃ መሣሪያ ማገናኛ) ቴክኖሎጂ መፈልሰፉ ተሰምቷል፡፡

በጣሊያን የተሰራው “ዜፊሮ” የተሰኘው ይህ መተግበሪያ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ካየናቸው ዘመናዊ መተግበሪያዎች ውስጥ አንዱ ነው።

ይሁንና እስከ አሁን ሥራ ላይ ከዋሉት ሌሎች መተግበሪያዎች የተለየና የላቀ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

አነስተኛ፣ በቀለማት ያሸበረቀ እና በትንፋሽ እንዲሰራ ተደርጎ የበለጸገው መሣሪያ በዘመናዊ ስልክ ቻርጅ መሰኪያ ላይ በመሰካት የሚሰራ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

መተግበሪያው በተጫነለት መቆጣጠሪያ አማካኝነት ስልኩን በእጅ በመነካካት እንደዋሽንት፣ ቫዮሊን እና ሌሎችም ድምፆችን በመቀያየር ለመጫወት እንደሚያስችል ተነግሯል።

የሙዚቃ መሣሪያዎቹን ትንፋሽን በመጠቀም መጫወት የሚያስችለው መተግበሪያው፤ በተገጠመለት የከንፈር እና የአየር ግፊት ሴንሰር አማካኝነት የትንፋሽ ኃይል መረጃን ወደ ተዘጋጀው መተግበሪያ ይልካል፡፡

ይህም የድምፁን መጠን፣ ርዝማኔ እና ቅላፄ ለማስተካከል እንደሚጠቅም ተገልጿል።

መሣሪያው ትንፋሽን በመጠቀም በስልኩ ስክሪን ላይ የሚታዩ ቁልፎችን ወይም ቀዳዳዎችን እንደአስፈላጊነቱ በጣት በመነካካት የፈለጉትን ዜማ መጫወት ያስችላል ተብሏል፡፡

ይህን መረጃ የሰሙ በርካቶች መተግበሪያውን በእጃቸው ለማስገባት ፍላጎት ማሳየታቸውም ተመላክቷል፡፡

መተግበሪያው በሚቀጥለው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መጀመሪያ ላይ ለገበያ እንደሚቀርብ የተገለጸ ሲሆን፤ ለመጀመሪያዎቹ ገዢዎች በ22 ዩሮ ይሻጣል መባሉን ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡

ለሌሎች ፈላጊዎች ደግሞ አንዱን መተግበሪያ በ42 ዩሮ አካባቢ ለመሸጥ ዋጋ መቆረጡ ተጠቁሟል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review