AMN – መስከረም 10 /2017 ዓ.ም
በደቡብ ሊባኖስ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ኃይል በእስራኤልና በሊባኖስ ድንበር ለአንድ ዓመት ገደማ ሲካሄድ የቆየው የተኩስ ልውውጥ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆም አሳስቧል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ኃይል ቃል አቀባይ አንድሪያ ቴኔንቲ ለሬውተርስ እንደገለጹት፤ በአካባቢው ያለው ውጥረት በከፍተኛ ሁኔታ መባባሱን እንደተመለከቱ ተናግረዋል።
በአካባቢው ሰማያዊውን መስመር ያለፈው ውጥረት እየጨመረ መምጣቱ ያሳስበናል ያሉት ቃል አቀባዩ፤ “ሁሉም ተዋንያኖች ግጭቱን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እናሳስባለን” ብለዋል።
ትናንት በቀኑ መገባደጃ ላይ የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች ደቡባዊ ሊባኖስ ላይ ከፍተኛ ጥቃት ፈጽመዋል።
ግጭቱ የተባባሰው በዚህ ሳምንት በሺህ የሚቆጠሩ የጥሪና ግንኙነት መሳርያዎች (ፔጀሮች) ፈንድተው 37 ሰዎችን ለህልፈት የዳረገውንና በሺህ የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎችን ያቆሰለውን ጥቃት ተከትሎ ነው።
በታምራት ቢሻው