በመሬት ስር የተገነቡ የእግረኛ መንገዶችን በአግባቡ ባልተጠቀሙ እግረኞች ላይ የቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል-የትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን

You are currently viewing በመሬት ስር የተገነቡ የእግረኛ መንገዶችን በአግባቡ ባልተጠቀሙ እግረኞች ላይ የቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል-የትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን

AMN-መጋቢት 13/2017 ዓ.ም

በመሬት ስር የተገነቡ የእግረኛ መንገዶችን በአግባቡ ባልተጠቀሙ እግረኞች ላይ የቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የአዲስ አበባ የትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን አስታውቋል።

በዚህም በሳምንቱ 645 እግረኞች በገንዘብ እና 466 ደንብ ተላላፊ እግረኞች ማህበራዊ ግልጋሎት በመስጠት መቀጣታቸው ተገልጿል።

በአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን የአራዳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በአራት ኪሎ አደባባይ የእግረኞች የመሬት ውስጥ መተላለፊያ መንገድ (Underpass) በማይጠቀሙ እና ተገቢ ያልሆነ የመንገድ አጠቃቀም በነበራቸው እግረኞች ላይ በግንዛቤ የተደገፈ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

የአራት ኪሎ አደባባይ የእግረኞች የመሬት ውስጥ መተላለፊያ (Underpass) ላይ እግረኞች መንገዱን በአግባቡ እንዲጠቀሙበት በሳምንቱ በተደረገው በማስተማር የተደገፈ ቁጥጥር መንገዱን በአግባቡ ባልተጠቀሙ 1 ሺ 111 እግረኞች ላይ የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክን ለመቆጣጠር በወጣው የሚንስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 557/2016 መሰረት ቅጣት እንደተጣለባቸው ተመልክቷል፡፡

የበጎ ፈቃደኛ ትራፊክ አስተናባሪዎችን ጨምሮ የጽ/ቤቱ የትራፊክ ቁጥጥር ባለሙያዎች አማካኝነት እግረኞች የመሬት ውስጥ መተላለፊያው እንዲጠቀሙበት በተደጋጋሚ ትምህርት እየተሰጠና ከዛ ባለፈ ቅጣቱ እየተጣለ እንደሚገኝ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ተክሌ ካሳዬ ገልጸዋል፡፡

የእግረኛ ቁጥጥር ስራው በሳምንቱ ሁሉም ቀናት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ማኀበራዊ ትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review