AMN – ጥር 2/2017 ዓ.ም
በቅርብ ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ ፍሰትና አጠቃላይ የፀጥታ ሁኔታ እንዲሁም ታላላቅ ፕሮግራሞችን ቁጥጥር ማድረግ የሚችሉ የድሮኖች ስምሪት እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ገለፁ፡፡
የፀጥታ ጥምር ኃይል በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ያለውን የፀጥታ ሁኔታን በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጧል።
ግምገማውን የመሩት ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የወንጀል መከላከል ስራውን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ የሚችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከ15 ቀናት በፊት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የከተማዋ ሰላምና ደህንነት ዘላቂ እንዲሆን የፀጥታ ጥምር ኃይሉ ተቀናጅቶ በመሥራቱ ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል፡፡
በዚህም አሁን ላይ በአዲስ አበባ ምቹ የፀጥታ ሁኔታ ያለበትና በቀጣይ በአገሪቱ የሚከበረው የጥምቀት በዓል እና የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ በሰላም እንዲጠናቀቁ ከወዲሁ ይህንን የሚመጥን ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል፡፡
በከተማዋ አልፎ አልፎ የሚገጥሙ የተሽከርካሪ እቃዎችና የሞባይል ስርቆቶች የሚስተዋሉ ስለሆነ ህዝቡ እና ቱሪስቶች ያለ ስጋት በነፃነት መንቀሳቀስ እንዲችሉ ችግሮቹን ለማስወገድ ጥምር የፀጥታ ኃይሉ በከፍተኛ ትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው በከተማዋ ወንጀል መቀነስ የቻለው በቀንና በማታ የቴክኖሎጂ አቅሞችን በመጠቀም ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ ከመላው ህብረተሰቡ፣ ከሰላም ሰራዊት እና ከደንብ አስከባሪዎች ጋር ተቀናጅቶ በመሰራቱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የሽብር ኃይሎች የከተማዋን ፀጥታ ለማደፍረስ በተለያየ መንገድ ያደረጉትን ሙከራ ጥምር የፀጥታ ኃይሉ በተቀናጀ መንገድ ማክሸፍ የቻለ በመሆኑ መሆኑን ያወሱት ኮሚሽነሩ የታጠቁ ኃይሎች በከተማዋ ውስጥ ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር የሚፈጥሩበት ዕድል ዝግ መሆኑንና የከተማዋ ፀጥታ እጅግ አስተማማኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መግለጻቸውን ከፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡