AMN-ጥቅምት 15/2017 ዓ/ም
በብሪክስ ጉባኤ ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታ በመነሳት በቀጣናው ሰላምና ፀጥታ ማስከበር ላይ ጉልህ ድርሻ እንዳላት መመላከቱን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ፡፡
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በሩሲያ ካዛን 16ኛው የብሪክስ ጉባኤ ሰፋ ያሉ ጉዳዮች የተዳሰሱበት መሆኑን በመግለጽ ከነዚህም ውስጥ የሰላምና ደህንነት ጉዳይ ቀዳሚው መሆኑን አመላክተዋል፡፡
አሁን ላይ በዓለም በተለያዩ ቀጠናዎች ግጭቶች እና ውጥረቶች የተበራከቱ መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዚህም ብዙዎች እየተጎዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በሌላ በኩልም አሁን እየመጣ ካለው ዲጂታል ዓለም ጋር በተገናኘ ከዳታ ስርቆት፣ ከሀሰተኛ መረጃ ስርጭት እና የጥላቻ ንግግሮች ጋር በተያያዘ ለዓለም ሰላም የራሱ ችግር እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የዓለም ፀጥታና ሰላምን የማጠበቅ ጉዳዮች በስፋት ተነስተው እንደተመከረባቸውም ገልፀዋል፡፡
የብሪክስ አባል ሀገራት በቅድሚያ በራሳቸው ውስጥ ያሉ ልዩነቶችን በማጥበብ የብሪክስን ውህደት እና ጥንካሬ ለማምጣት የሚያስችሉ መግባባቶችን ማጎልበት ላይ በዋናነት ምክክር መደረጉን አመላክተዋል፡፡
በዓባል ሀገራቱ መካከል ልዩነቶች ካሉም ከጋራ ጥቅሞች የማይበልጡ ስለሚሆኑ በሀገራት ማካከል እነዚህ ልዩነቶችን የመፍታት አስፈላጊነት ላይ ውይይት መደረጉን አንስተዋል፡፡
ብሪክስም እንደ አንድ ቤተሰብ በመተጋገዝ የብሪክስ ዓባላትን መቀራረብ የሚያጎለብቱ ሥራዎችን መሥራትና ከዚህም አልፎ ዓባል ሀገራቱ ለዓለም ሰላም የጋራ አስተዋፅዖ ማበርከት በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ተመክሯል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታ በመነሳትም በቀጣናው ሰላምና ፀጥታ ማስከበር ላይ ጉልህ ድርሻ እንዳላት መነሳቱን ነው አምባሳደር ሬድዋን የጠቆሙት፡፡
በጉባኤው መድረክ በጋራ የተነሱ ጉዳዮችንም በተናጠል ከተለያዩ ሀገራት ጋር በተደረገ የሁለትዮሽ ምክክር፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ መሆኑን ነገር ግን ያለችበት ቀጣና ችግር ያለበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የጎላ ድርሻ እንድትጫወት ብዙ ሀገራት አብረዋት መስራት ፍላጎት እንዳላቸው መግለፃቸውንም አመላክተዋል፡፡
በታምራት ቢሻው