AMN-ጥር 16/2017 ዓ.ም
በስራ ቅጥር ሽፋን በህገወጥ አለምአቀፍ የሰው አዘዋዋሪዎች ወደ ማይናማር ተወስደው ችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለመታደግ መንግስት እያደረጋቸው ያሉ ጥረቶች መቀጠላቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ከሰሞኑ በህንድ ኒውዴልሂ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሚሲዮን የልዑካን ቡድን ወደ ታይላንድ በመላክ በእስር ላይ ይገኙ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች እንዲለቀቁ ማድረጉን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ማይናማር ውስጥ ከነበሩት ከስቸጋሪ ሁኔታ አምልጠው ወደ ታይላንድ የሚገቡ ስደኞች ህጋዊ ዶክመንት ባለመያዛቸው ለእስር ተዳርገው እንደነበር የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል።
በኒውዴልሂ የኢትዮጵያ ሚስዮን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ባደረገው ጥረት 38 ኢትዮጵያዊን ከእስር ተለቀው ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ መደረጉ ታውቋል።
ኢትዮጵያውያንን በህክምና እና በኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ስራ ታገኛላችሁ በሚል የተሳሳተ መረጃ ወደ ታይላንድ ከዛም ወደ ማይናማር እየተወሰዱ ህገወጥ ስራዎችን እንዲፈፅሙ የሚደረጉ ሲሆን ለከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተዳረጉ እንደሚገኙ ተመላክቷል።
ችግሩን ለመቅረፍ መንግስት ብሄራዊ ኮሚቴ አቋቁሞ እየሰራ እንደሚገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።