ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም በዛሬው ዕለት በመላው ኢትዮጵያ “የኅብር ቀን” “ኅብራችን ለሰላማችን” በሚል መሪ ቃል ተከብሮ ውሏል።
ቀኑ ብዝኃነትን በሚያጎላ እንዲሁም በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና ፓለቲካዊ ጉዳዮች በአብሮነት የዘለቁ እሴቶችን በሚያንፀባርቁ ተግባራት ተከብሯል።
የኅብር ቀን ኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን የሚያፀና፣ ብዝኃነታችንን የጥንካሬያችን ምንጭ የሚያደርግ፣ አንዳችን ለሌላችን በማሰብ ከብረት የጠነከረ አንድ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የሚፈጥር እሳቤ ነው።
በኢትዮጵያ የተለያዩ ማንነቶች፣ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ ሃይማኖቶች እና ልማዶች ቢኖሩም በእነዚህ ልዩነቶች ውስጥ የሚያመሳስላቸው ኢትዮጵያዊ ማንነት አላቸው።
ዛሬ የኅብር ቀንን ስናከብር ሀገራችን ኢትዮጵያ በኅብር የተገነባች እና በጋራ መሥዋዕትነት ተጠብቃ የቆየች መሆኗን ወደ ኋላ መለስ ብለን በማሰብ ነው።
እጣፈንታችን በእጅጉ የተሳሰረ መሆኑን ይበልጥ በመገንዘብ አብሮነታችንን የሚፈታተኑ ተግባራት እና አስተሳሰቦችን ለመታገል ቁርጠኝነታችንን የምናድስበት ዕለት መሆን ይኖርበታል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በደም፣ በታሪክ፣ በሃይማኖት፣ በሥነ-ልቦና፣ በባህል እና በሌሎችም ማኅበራዊ እሴቶች የተጋመደ የአንድ ታላቅ ሀገር ሕዝብ ነው።
ይህ ሕዝብ የትናንት ማንነቱ፣ የዛሬ ኅልውናው እና የወደፊት ዕጣ ፈንታው የተሣሠረ በመሆኑ የባህላችን እሴት፣ የአይበገሬነታችን ምንጭ የሆነው ኅብረ ብሔራዊነቱን አጥብቆ መቀጠል አማራጭ የሌለው መንገድ ነው።
መከፋፈል እና መለያየት እንደ ሕዝብ እና ሀገር ከማሳነስ በስተቀር የሚያመጣልን ትርፍና ድል የለውም።
ኢትዮጵያውያን በኅብር ሀገር ገንብተናል፤ በአብሮነት ሀገራችንን ከየትኛውም ወራሪ ለመጠበቅ እና ነፃነታችንን በራሳችን መወሰን እንደምንችል በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች አሳይተናል።
አባቶቻችን አብረው ዘምተው፣ አብረው ሞተው፣ አብረውም ኖረው ነፃ ሀገር አስረክበውናል፤ እኛም የአባቶቻችንን የጀግንነት እና የአብሮነት ታሪክ ለማስቀጠል እና ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ግደታችንን እንወጣ።
AMN – ጳጉሜን 4/2016 ዓ.ም
በዮናስ በድሉ