በመዲናዋ በከተማ ግብርና ዘርፍ የተሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቁጥር 511 ሺህ መድረሱን የአዲስ አበባ ከተማ አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽነር ባዩ ሽጉጤ ገለጹ፡፡
ኮሚሽነር ባዩ ሽጉጤ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በከተማ ግብርና ዘርፍ የተደረገው የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ የኑሮ ውድነት ለማረጋጋትና የገበያ ትስስር በመፍጠር ላይ ውጤት እያመጣ መሆኑን ጠቁመዋል።
የከተማ ግብርና በሰብል ልማት ዘርፍ በአዲስ አበባ ተግባራዊ መሆን የጀመረው በ2012 ዓ.ም ነው ብለዋል፡፡
በ2014 ዓ.ም ደግሞ ከተማ አቀፍ የከተማ ግብርና ንቅናቄ በማካሄድ በተለይ በጓሮ አትክልት ልማት በርካታ ተጠቃሚዎች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
በ2015 በጀት ዓመትም በብዛት በሰብል ልማት ላይ ያተኮረ የነበረውን የከተማ ግብርና በሌማት ትሩፋት ፕሮግራም የእንስሳት ዘርፍን እንዲያካትት መደረጉን አውስተዋል፡፡
በመሆኑም አሁን ላይ በመዲናዋ 511 ሺህ የኅብረተሰብ ክፍሎች በጓሮ አትክልት፣ በዶሮና በወተት ላም እርባታ፣ በንብ ማነብና መሰል የከተማ ግብርና ዘርፎች ተሰማርተው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ባለፉት ጊዜያት የከተማ ግብርናን በውስን ቦታ ተግባራዊ በማድረግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚቻል ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር የተለያዩ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አውስተዋል፡፡
በዚህም በኅብረተሰቡ ዘንድ በትንሽ ሥፍራ የከተማ ግብርናን ተግባራዊ በማድረግ ከራስ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ትርፋማ መሆን እንደሚቻል በአስተሳሰብ ደረጃ ለውጡ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓትም የሰብልም ሆነ የእንስሳት ምርቶችን ለመዲናዋ ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት ለማቃለል የራሱን ጉልህ ሚና እያበረከተ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በ2016 ዓ.ም ከዚህ በፊት ዘርፉን የተቀላቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የማስቀጠል ብሎክን መሠረት ያደረገ 249 ሺህ 800 አዳዲስ ተጠቃሚዎችን ለማካተት መታሰቡን ገልፀዋል፡፡
በአዲስ አበባ ለከተማ ግብርና የሚሆን ሰፊ መሬት መኖሩን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፤ ይህን ለማልማት የሚያስችል ከለጋሽ ድርጅቶች የሚገኘውን ሳይጨምር በከተማ አስተዳደሩ ብቻ ከ 500 ሚሊየን ብር በላይ በጀት መያዙን ተናግረዋል፡፡
የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ደግሞ መንግሥት ዘመናዊ የግብርና ምርት ግብዓቶችን የማቅረብና ሼዶችን የመገንባት ሥራን ከዚህ በፊት ከነበረው በበለጠ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራበት አመላክተዋል፡፡
ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!
YouTube ➲ http://bit.ly/3itThRr
Telegram ➲ http://bit.ly/3W4puw9
Facebook ➲ https://bit.ly/3CJVgI8
Twitter ➲ http://bit.ly/3IKQ3TZ