AMN-ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም
ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ፡፡
መንግሥት በኢንዱስትሪ ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለማቃለል ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል አንዱ ከሁለት ዓመት በፊት በይፋ በሀገር አቀፍ ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ስራ የገባው የኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ ተጠቃሽ ነው።
ንቅናቄው የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም የማሳደግ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ፣ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ፣ የሀገር ውስጥ አምራቾችን የእርስ በርስ ትስስር በማጠናከር እና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ወደ ወሳኝ ምዕራፍ በማሸጋገር ያለመ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገልፀዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።
ሀገራዊ ንቅናቄው የታለመለትን ዓላማ እያሳካ ስለመሆኑ ለዘርፉ የሚቀርቡ የብድር፣ የውጭ ምንዛሪና የሊዝ ፋይናንስ አገልግሎቶችን ማሳደግ በመቻሉና የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም በማደጉ ዘርፉ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ተጨባጭ አስተዋፅኦ ወደማበርከት እየተሸጋገረ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራ ፣የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማሳደግ፣ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት እና ሌሎች በዘርፉ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች ማሳያዎች መሆናቸውን ሚኒስትሩ መናገራቸውን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡