በዓሉን ስናከብር ያለንን በማካፈል ፤ የታረዙትን በማልበስ እና የታመሙትን በመጠየቅ ሊሆን ይገባል-የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ

You are currently viewing በዓሉን ስናከብር ያለንን በማካፈል ፤ የታረዙትን በማልበስ እና የታመሙትን በመጠየቅ ሊሆን ይገባል-የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ

AMN – ታኀሣሥ 28/2017 ዓ.ም

የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

ሙሉ መልዕክቱ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

የ2017ዓ.ም የጌታትንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓልን አስመልክቶ ከአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የተላለፈ የመልካም ምኞት መልዕክት

በመላው ዓለም የምትገኙ የክርስትና ዕምነት ተከታይ ኢትዮጵያዉያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በቅድሚያ በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ታህሳስ 29 ቀን ለ2017 ለሚከበረው ለጌታችንና ለመድሃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት መታሰቢያ በአል በሰላም አደረሳችሁ በማለት የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መልካም ምኞቱን ይገልጻል፡፡

የጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ለሰው ልጆች ሁሉ “ታላቅ የምስራች” ተብሎ በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ሲበሰር በዋናነት ሁለት ታላላቅ ጉዳዮች ተከናውነዋል፡፡

የመጀመሪያው በጌታ መወለድ ምክንያት ሰዎችን ሁሉ ከሃጢያትና ከሞት የሚያድን መድሃኒት መገኘቱን ሲሆን ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም በበረት ውስጥ ሲወለድ እሱ የዓለም ፈጣሪ እና ጌታ ሆኖ ሰውን ዝቅ ብሎ የማገልገልን ምሳሌነት የተወልን መሆኑን ያስታውሰናል፡፡ ይህን በዓል ስናከብር ክርስቶስ ከሃጢያትና ከሞት የሚያድነን መሆኑን በውል በመገንዘብና በሰዎች መከካል ስንኖርና ስናገለግል በትህትናና ለሰዎች ክብር በመስጠት መሆኑን መዘንጋት የለብንም ፡፡

በተጨማሪ የልደት በዓሉ የሚያስተምረን ቁም ነገር ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ _ የበደለውን የሰው ልጅ ይቅር ካለውና የመዳን ተስፋ ከሰጠው እኛም ይህንን በዓል ስናከብር የበደሉንን ይቅር በማለት ፣ ያጠፋነውን በማስተካከልና በማረም ፣ ጥላቻን በማስወገድ ፣ ፍቅርን ለሰው ልጆች በመስጠት ሊሆን ኣንደሚገባ የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በትህትና ያሳስባል፡፡

ያለንን ማካፈል ፤ የታረዙትን ማልበስ እና የታመሙትን መጠየቅ ዘመናትን ተሻግሮ የመጣ አብሮ የመኖር ኢትዮጵያውያን እሴቶቻችን ስለሆኑ አነኝህ እሴታችን ተጠብቀውና ተጠናክረው ለትውልዱ እንዲተላለፉ ካለን በማካፈል እና እርስ በርስ በመደጋገፍ የአብሮነትና የወንድማማችነት ባህላችን ሆኖ እንዲቀጥል ልንሰራ ይገባል፡፡

ክርስቶስ ሕይወት እና አስተምህሮ አገልጋይነት በመሆኑ ይህንን ከጌታ የተማርነውን እራስን ለሌሎች መስጠትን፣ ትህትና እና የአገልጋይነት ባህሪይ በመላበስ የማገልግል ምሳሌነትን ባለንበት የሃላፊነት ቦታ ሁሉ ልንተገብረው እንደሚገባ ይህ በዓል በአንክሮ ያሳስበናል፡፡

ጉባኤያችን ከዚህ ቀደም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያ ውስጥ ለሚገኙ ወገኖቻችን ሰበዓዊ ድጋፎችን ሲያደርግ የቆዬ ሲሆን ወደ ፊትም ይህንን ተግባር ኣጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል በዚህ በዓልም በሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮዓዊ ችግሮች ምክንያት በተለያዩ መጠለያ ውስጥም ይሁን በየአከባቢያችን የሚገኙ አቅመ ደካሞችን እና አረጋውያንን ልናግዛቸው ልንደግፋቸው ይገባል፡፡

የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በድጋሚ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ በዓሉ የሰላም፤ የፍቅር ፣ የመከባበር ፣ የወንድማማችነት እንዲሁም ሀገራችን ወደ ዘላቂ ነላም የምትሸጋገርበት ጊዜ እንዲሆን መልካሙን ሁሉ እንመኛለን፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review