በጤናው ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት በከተማዋ የጤና ሽፋን ፍትሃዊ ተደራሽነት እያደገ ነው – የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ

You are currently viewing በጤናው ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት በከተማዋ የጤና ሽፋን ፍትሃዊ ተደራሽነት እያደገ ነው – የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ

AMN – ጥር- 20/2017 ዓ.ም

በለውጡ አመታት በጤናው ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት በከተማዋ የጤና ሽፋን ተደራሽነት ማደጉን እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ መምጣቱን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ዮሃንስ ጫላ እንዳሉት በለውጡ አመታት የመዲናዋን የጤና አገልግሎት ፍትሃዊ ተደራሽነት የሚያሰፉ ስራዎች ተከናውነዋል።

በዚህም በከተማዋ የጤና ሽፋን ተደራሽነትን ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰው ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።

የጤና አገልግሎት ፍትሃዊ ተደራሽነትና ጥራትን ለማስጠበቅ ነባር ሆስፒታሎችን የማደስና የማስፋፋት እንዲሁም ከፍተኛ አቅም ያላቸው አዳዲስ ግንባታዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ከለውጡ በፊት በጤና መድህን አገልግሎት በ10 ወረዳዎች የሚገኙ ከ60 ሺህ የማይበልጡ ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንደነበሩ አንስተው አሁን ላይ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን መድረሱን ተናግረዋል።

እናቶችና ህፃናት፣ አስተኝቶና ፅኑ ህክምና ላይ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው በከተማ ደረጃ እንደ ሀገር በ2030 በዘላቂ ልማት ግቦች ለመድረስ የተቀመጡ ግቦችን ቀድሞ ማሳካት ተችሏል ነው ያሉት።

በ2026 በአፍሪካ ህፃናትን ለማሳደግ ተመራጭ ከተማ የማድረግ ዓላማን ይዞ መተግበር የጀመረው የቀዳማይ ልጅነት መርኃ ግብር ለአፍሪካ ተሞክሮ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የቀዳማይ ልጅነት መርኃ ግብር ከጤና ቢሮ በተጨማሪ በሌሎች ዘርፎች የሚደገፍ መሆኑን ጠቅሰው በጤናው ዘርፍ ብቻ ለቀዳማይ ልጅነት መርኃ ግብር ከ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ከተማ አስተዳደሩ መመደቡን ገልፀዋል።

በለውጡ አመታት በከተማ አስተዳደሩ ስር ያሉ ሁሉም ሆስፒታሎች ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ስርዓት እንዲጠቀሙ ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ከተማ አስተዳደሩ በውጤታማነት እያከናወናቸው ከሚገኙ ስራዎች መካከል የጤና ዘርፍ አንዱ መሆኑም ተመላክቷል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review