በፍጥነት ወደ ግንባታ በመግባት መምህራን የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ሁሉም ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል ተባለ

You are currently viewing በፍጥነት ወደ ግንባታ በመግባት መምህራን የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ሁሉም ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል ተባለ

AMN – መስከረም 8/2017 ዓ.ም

በፍጥነት ወደ ግንባታ በመግባት መምህራኑ የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ሁሉም ባለድርሻ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ እና የቢሮ ኃላፊ ተወካይ ወ/ሮ ታጋይቱ አባቡ አስገነዘቡ።

የመኖሪያ ቤት የሌላቸው መምህራን በማህበር ተደራጅተው የቤት ባለቤት እንዲሆኑ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ተገምግመዋል።

በመርሀ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ማኔጅመንት አባላትን ጨምሮ የመምህራን ማህበር አመራሮች እንዲሁም የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር እና የህብረት ስራ ኮሚሽን የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ እና የቢሮ ኃላፊ ተወካይ ወ/ሮ ታጋይቱ አባቡ፤ የመኖሪያ ቤት የሌላቸው መምህራን ተደራጅተው የቤት ባለቤት እንዲሆኑ እየተሰሩ የሚገኙ ተግባራትን በመገምገም በቀጣይ በፍጥነት ወደ ግንባታ በመግባት መምህራኑ የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ሁሉም ባለድርሻ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ድንቃለም ቶሎሳ በበኩላቸው ባለድርሻ አካላት ከምዝገባ ጀምሮ እስካሁን እያደረጉ ለሚገኘው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው፣ በቀጣይ ማህበራቱን በማደራጀት ወደ ቀጣዩ ስራ ማምራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

የመንግስት ሰራተኞች የጋራ ህንጻ የመኖሪያ ቤት ህብረት ስራ ማህበራት አደረጃጀት እና አፈጻጸም ደንብ ቁ.129/14 መሰረት መምህራኑን ለማደራጀት የተከናወኑ ተግባራት ሪፖርት በህብረት ስራ ኮሚሽን አማካይነት ቀርቦ ውይይት መካሄዱን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በውይይቱ ማጠቃለያ እስካሁን የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን 30 በመቶ ቆጥበው ወደ መደራጀት ለመግባት የተመዘገቡ መምህራንን ወደ ግንባታ እንዲገቡ ከባንክ ጋር የማስተሳሰር እና መሬት የማቅረብ ስራ በሚመለከታቸው አካላት መሰራት እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

እየቆጠቡ ለመደራጀት የተመዘገቡትን የቁጠባ ባህላቸውን አሳድገው ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ እንዲገቡ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም ነው የተመላከተው።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review