በ2016/17 የምርት ዘመን ምርት እንዳይባክን የቅድመ ዝግጅት ሥራ በትኩረት መሠራቱ አመርቂ ውጤት አስገኝቷል፦ የግብርና ሚኒስቴር

AMN – ታኅሣሥ 4/2017 ዓ.ም

በ2016/17 የምርት ዘመን ምርት እንዳይባክን የቅድመ ዝግጅት ሥራ በትኩረት መሠራቱ አመርቂ ውጤት ማስግኘቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በምርት ዘመኑ በ20.4 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ላይ ከለማው የመኸር ሰብል ውስጥ እስከ አሁን በ11.25 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ላይ የሚገኘው ሰብል መሰብሰቡን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኢሳይያስ ለማ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል በሰጡት መረጃ፣ እስካሁን ያለው አፈፃፀም ከ50 በመቶ በላይ መሆኑን እና ከዚህም ውስጥ 165 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተወቅቶ ወደ ጎተራ መግባቱን ገልጸዋል።

ሀገሪቱ የተለያየ ዓይነት ሥነ-ምኅዳር ያላት በመሆኑ፣ በጥቅምት ወር ሰብል የሚሰበስቡ እና ሰብል በመስከረም ወር የሚዘሩ እንዳሉ የገለጹት ባለሙያው፣ በኅዳር እና በታኅሣሥ ወራት ግን በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ሰብሎች የሚደርሱበት እና የሚሰበሰቡበት ወቅት እንደሆነ አመላክተዋል።

አሁን ላይ የአየር ንብረቱ ምቹ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህ ወርም በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ሰብል የሚደርስበት እና ምርት የሚሰበሰብበት በመሆኑ በቀጣይ ሳምንታት የአሰባሰብ ሂደቱ ወደ 80 በመቶ ከፍ እንደሚልም አብራርተዋል።

ለአርሶ አደሩ ምርቱን በወቅቱ መሰብሰብ፣ የደረሰ ሰብልን ማሳ ላይ እንዳያቆይ እና እንዳይዘናጋ በየሳምንቱ በየደረጃው በባለሙያ በሚደረጉ ክትትሎች የተጠናከረ ሥራ መሠራቱንም አንሥተዋል።

ማሽነሪዎች በማይደርሱባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሮች የቤተሰብ ጉልበትን ጨምሮ በልማት ቡድን፣ በትምህርት ቤቶች፣ በዕድር እንዲሁም በየመንደሩ ያላቸውን ባህላዊ አደረጃጀቶች በመጠቀም ተባብረው ምርት እንዲሰበስቡ በመደረጉ ጥሩ ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።

ወቅቱ ሰብል ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ክስተቶች ያልነበሩበት እና መልካም የሚባል የአየር ሁኔታ የነበረበት መሆኑን ያነሡት አቶ ኢሳይያስ፣ ተሰብስቦ እየተወቃ ካለው ሰብል አንፃር በምርት ዘመኑ ለመሰብሰብ የታቀደውን 608 ሚሊዮን ኩንታል እና ከዚያም በላይ የመኸር ሰብል መሰብሰብ እንደሚቻል ጠቁመዋል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review