“‘ቤቱ ይጠብባል፤ ይቀዘቅዛል፤ መቀመጫየለም’ ከሚል ስጋት ወጥተን በዓሉን በደስታ ለማክበር ተዘጋጅተናል”

በኮሪደር ልማት ምክንያት አዲስ ቤት ያገኙ ወ/ሮ ብዙነሽ ተካ

ኢትዮጵያ የክረምት ወቅት የሚፈጥረው ዝናባማ፣ ደመናማ እና ብርዳማ አየር አሳልፋ ብርሃናማ የሰማይ ድምቀትን የምትላበስበት፣ የምድሯ ልምላሜ እና የአደይ አበባ ፍካትም ለምድሪቷ ፀጋን የሚያጎናፅፍበት ወር ነው፤ መስከረም፡፡ በዚህ ወር የመጀመሪያ ቀን በሕዝቧ   የአኗኗር  ባህል  ውስጥ   የኖረ እና የዳበረ በዓል ይከበራል፤ አዲስ ዓመት። ባህላዊ ጨዋታዎች፣ ዜማዎች በሃገሬው ህይወት ላይ ይገለጣል፤ ይደመጣል እንዲሁም ይሸተታል፡፡ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያውያን ሕፃን አዛውንት፣ ሴት ወንድ ሳይሉ በደስታ፣ በፍቅር ተሰባስበው  እንኳን አደረሰህ! አደረሰሽ! መልካም አዲስ አመት! የሰላምና የጤና ዓመት ይሁንልን!  እየተባባሉ መልካም ምኞታቸውን ይገላለፃሉ።

አዲስ ዓመት ሰዎች አዲስ ተስፋ የሚሰንቁበት፣ ከአሮጌው ዘመን በመማር አዲስ እቅድ የሚያወጡበት፣ ጠንክረው በመስራት ህይወታቸውን ለመለወጥ ታጥቀው የሚነሱበት ወቅት ነው፡፡ በተለይ በኑሯቸው ላይ አዎንታዊ ለውጥ አምጥተው ለሚቀበሉት አዲስ ዘመን የሚፈጥረው የደስታ ስሜት እጥፍ ድርብ ነው።

ወይዘሮ ሳባ አሳምነው ትውልድና እድገታቸው በፒያሳ በተለምዶ ሰራተኛ ሰፈር ነው፡፡ ከ30 ዓመታት በላይም በአካባቢው ኖረዋል፡፡ ሁለት በሁለት ሜትር በሆነች ጠባብ፣ ከእንጨትና አፈር በተሰራች፣ ከእርጅና ብዛት ልትወድቅ የዘመመች እንዲሁም ዝናብ ጠብ ባለ ቁጥር በጎርፍ የሚሞላ መኖሪያ ቤት ውስጥ ኑሯቸውን ሲመሩ ቆይተዋል።

በኮሪደር ልማት ምክንያት አዲስ ቤት የተሰጣቸው ወ/ሮ ሳባ አሳምነው ከጎረቤቶቻቸው ጋር

ከሁሉ የባሰው ደግሞ ሶስት የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች ከቤታቸው በር ፊት ለፊት መኖሩ መሆኑን የሚገልጹት ወይዘሮ ሳባ፤ “ሽታውና እርጥበቱ ለበሽታ ያጋልጣል፡፡ ነፍሳቶቹ ጭስ የማያርቃቸው የቅርብ ጎረቤቶቼ ናቸው፤ ቤት ከዋልን ቀን ሽታውን ለመከላከል በር ዘግተን ነው የምንውለው፡፡ ቤት ውስጥ ምግብ መመገብ ይከብድ ነበር፤ ጎዳና ላይ ከመውደቅ ተብሎ ነው የኖርነው፡፡ ‘ቤቱ ቤት አልነበረም’ ማለት ይቀለኛል” ሲሉ አኗኗራቸው ምቾት የራቀው እንደነበር ይናገራሉ፡፡

በዚህ ኑሮ ላይ እናታቸው ሲሞቱ የቤተሰብ ሃላፊነቱን መሸከም እንዳለ ሆኖ ቤቱ ከእርጅና ብዛት በላያቸው ላይ ሊወድቅ  ተቃረበ። በዓል የበለጠ ደስታን እንደሚሰጣቸው የሚናገሩት ወይዘሮዋ፣ “ሰዎች እንደ አቅማቸው ቤታቸውን ቀለም በመቀባት፣ ምንጣፍ በማንጠፍ አስውበውና አስጊጠው በጉጉት ይጠባበቃሉ። እኔ ቤት ግን በዓላቱ ቢፈራረቁም ደስተኛ ሆኜ አላውቅም። በተለይ በአዲስ ዓመት ከክረምቱ ዝናብ ጋር ተያይዞ ከላይ ሲያፈስ ከታች ጎርፉ ሲገባ ቤት ይሁን ውጭ እንዳይለይ ያደርገዋል። ጎረቤቶቼ መጥተው ምን ላይ ተቀምጠው እንደማስተናግዳቸው ይጨንቀኛል፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንግዳ ባይመጣብኝ ምርጫዬ ነበር፡፡ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ‘እንደ ዘመኑ የእኔንም ህይወት ቀይረው’ እያልኩ ነበር የምለምነው” ሲሉ በርካታ ዓመታትን ያሳለፉበት የመኖሪያ ቤታቸው ምን ያህል ለመኖሪያ ምቹ እንዳልነበር ነግረውናል፡፡

ጊዜ የማይፈታው ነገር የለምና በኮሪደር ልማቱ ምክንያት ተነስተው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ለመኖሪያ ምቹ የሆነ ባለ 1 መኝታ ቤት ተሰጥቷቸዋል፡፡ የዝግጅት ክፍላችንም በአዲሱ ቤት ያላቸውን ስሜት እንዲሁም አዲስ ዓመትን እንዴት ሊያከብሩ እንደተዘጋጁ ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ጎራ ባልንበት ወቅት ፈገግ ብለው “እንግዳ ሲመጣ በደስታ እንድቀበል ያደረገኝ ፈጣሪ ይመስገን” በማለት ከተቀመጡበት ተነስተው ሶፋው ላይ እንድንቀመጥ ጋበዙን።ደስታቸውን ለመግለፅ ቃላት አንሷቸዋል፤ “በንፁህ ቤት ተኝቶ ሲነጋ ቢሞት”ስ የሚል ቃልን ብቻ ተናገሩ፡፡ አይናቸውም የደስታ እንባን አቀረረ፡፡

በኮሪደር ልማቱ ሲነሱ የተሰጣቸው ምትክ ባለ 1 መኝታ ቤት እጅግ ማራኪ፤ እይታን የሚስብና ʽመኖርስ እንደዚህ ባለ ቤትʾ እንዲሉ አስገድዷቸዋል፡፡ የወይዘሮዋ አዲሱ ቤት መኝታ፣ የምግብ ማብሰያ፣ መመገቢያ ለየብቻው አለው። “በዓላት ሲመጡ ደስታ ይርቀኝ ነበር፤ አሁን ደስተኛ ሆኛለሁ፡፡ በንፁህ፣ በአዲስ እንዲሁም ለእይታ በሚማርክ ቤት የማዘጋጀው ባይኖረኝም ጥሬ ቆልተን በደስታ እናሳልፈዋለን፡፡ ይህ ለእኔ መታደል ነው፡፡ እኔን ያየ ፈጣሪ በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ያሉትንም ይመልከታቸው ነው የምለው” ሲሉ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀውልናል።

ከሰራተኛ ሰፈር ሲነሱ ብዙ ዓመታትን አብረዋቸው ያሳለፉ ጎረቤቶቻቸው አንድ አካባቢ ቤት እንደተሰጣቸው የሚናገሩት ወይዘሮ ሳባ፤ በፊት የነበረው ከጎረቤት ጋር በዓል ማክበሩም ይቀጥላል፡፡ እየኖርኩ ያለሁት ብዙ ዓመት የማውቀውን ሰፈር ለቅቆ እንደሄደ ሰው አይደለም፡፡ መጠራራቱ፣ ተሰባስቦ እያወጉ ቡና መጠጣቱ፣ መመራረቁ፣ ሳቅና ጨዋታው አልተለየንም፡፡ በአዲሱ ቤታችንም አብረውኝ ከመጡት እና ከአዳዲስ ጎረቤቶቻችን ጋር በመሆን በፊት ከነበረው በበለጠ በደስታና በሃሴት እየኖርን ነው፡፡

የኢትዮጵያውያን ባህል ሰብሰብ ማለትን የሚወድ ነው፡፡ በህብረትና አንድነት መቆም ከጥንት የቆየ ልማድ ነው፡፡ ቤታችን በሰዎች ይደምቃል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ የተሰጠን ቤት ምቹ ነው። በአዲስ ቤት ሆኖ በዓል ማክበር የተለየ ስሜት አለው፡፡ ለውጡ የተሻለ ነገር ይዞልን መጥቷል። ከዚህ በፊት ጠባብ የነበረው ቤት በሰፊ ቤት ተቀይሯል፡፡ ከጎረቤትና ዘመድ አዝማድ ጋር ተሰባስበን በደስታና በደመቀ ሁኔታ በአዲሱ ቤት አዲስ ዓመትን እናከብራለን፡፡ ታላቅ ደስታንም ፈጥሮልናል ሲሉ በሃሴት ተሞልተው ይናገራሉ፡፡

ወይዘሮ ሳባ 2016 ዓ.ም በህይወታቸው ትልቅ ለውጥ ያዩበት ዓመት ነው። “የማያልቅና የማያልፍ ሲሳይን ሰጥቶኝ አልፏል። ከወደቅኩበት አንስተውኛል፤ ፀጋ ነው ያለበሱኝ፤ እግዚአብሔርም ፈፅሞልኛል፤ የከተማ አስተዳደሩም ላደረገልን ሁሉ ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው” ሲሉ ምስጋናቸውን አቅርበው ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ሌላኛዋ የልማት ተነሺ ወይዘሮ ብዙነሽ ተካ በፒያሳ አካባቢ በተለምዶ በሰራተኛ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለ40 ዓመታት ኖረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 አዲስ ቤት ተሰጥቷቸው እየኖሩ ይገኛሉ፡፡ በርካታ ዓመታት የህይወትን ውጣ ውረድ ያሳለፉበት ቤት ምቾት የራቀው፣ ክረምት በመጣ ቁጥር ከላይ ዝናብ፣ ከታች ጎርፍ ይፈራረቁባቸው   ነበር፡፡  “ኑሮ  ካሉት መቃብርም ይሞቃል” እንደሚባለው ፈተናዎችን ሁሉ ችለው እንደኖሩበት ያለፈውን ህይወት በሀዘኔታ ገልጸውልናል፡፡

በኮሪደር ልማት ምክንያት አዲስ ቤት አግኝተው በዓልን በጥሩ ስሜት ለማክበር የተዘጋጁት ወ/ሮ ብዙነሽ ተካ

ሰባት የቤተሰብ አባላት በአንድ ላይ ሆነው እንደኖሩ የሚናገሩት ወይዘሮ ብዙነሽ፤ “ከቤታችን በስተጀርባ የቦታው አቀማመጥ ከፍ ያለ ስለነበር ዝናብ ሲዘንብ ጎርፉ ቀጥታ እኛ ቤት ውስጥ ነው የሚገባው። ዝናብ የዘነበ ቀን እንቅልፍ የለንም፡፡ የልጅ ልጆቼን ጎርፍ እንዳይወስድብኝ በስጋት ነው የኖርኩት፡፡ መፍትሄ ይሆን ዘንድም የመኝታ ቤቱን ግድግዳ በእንጨት በመቦርቦር ለጎርፉ መውረጃ ለቀቅን፤ አንዱ ቤት ውስጥ መኝታችንንም መመገቢያችንንም በማድረግ ነበር የምንኖረው።

አዲስ ዓመትን ስናከብርም መሬቱ ከመርጠቡ የተነሳ በጣም ይቀዘቅዘን ነበር፤ እንግዳም ሲመጣ ለማስተናገድ እንሳቀቅ ነበር። ቅዝቃዜውንና ጭቃውን ለመቋቋምም ብዙ ላስቲክና ምንጣፍ ለመግዛት ወጪ እናወጣለን” ሲሉ የማያልፍ ጊዜ እና የማይነጋ ሌሊት እንደሌለ ይናገራሉ፡፡

 “አሁን ታሪክ ተቀይሯል” የሚሉት ወይዘሮ ብዙነሽ፤ ችግራችንን አይቶ ያለፈው ዓመት የተባረከ እድልን አደለን፡፡ ፋሲካንም በአዲስ ቤት ነበር ያከበርነው፤ አዲስ ዓመትንም በሰፊ፣ በሚያምርና በንፁህ ቤት እናከብራለን። የበፊቱን ቤት ከአሁኑ ጋር ማነፃፀር የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት አለው” ይላሉ፡፡ 

“በጎርፍ ከሚጥለቀለቅ ቤት ወደ አዲስና ለመኖር ወደማያሰጋ ቤት ተሸጋግረናል። መጭውን ዘመን ‘ይባርክልን’” ሲሉም ከነቤተሰቦቻቸው ደስተኛ መሆናቸውን አንገታቸውን ቀና አድርገው ወደ ሰማይ እያዩ ፈጣሪያቸውን በማመስገን ገልፀውልናል፡፡

አዲስ ዓመትን በአዲስ ቤት ማክበር ከዚህ በፊት ለፋሲካ ስናከብር ከነበረው ደስታ የበለጠ ያደርገዋል፡፡ በዓላትን ተሰባስቦ ማክበር የኢትዮጵያውያን  ባህል ነው፡፡ እኛም “ቤቱ ይጠብባል፤ ይቀዘቅዛል፤ መቀመጫ የለም” ከሚል ስጋት ወጥተን በዓሉን በደስታ ለማክበር ተዘጋጅተናል ሲሉ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የደስታና የፍቅር እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

ልክ እንደ ስሟ፣ ባላት ሚና እና በሚመጥናት ደረጃ ልክ አይደለችም እየተባለች ስትነሳ የነበረችው አዲስ አበባ በ2016 በጀት ዓመት በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች በተከናወነው የኮሪደር ልማት ገፅታዋ እጅጉን ተቀይሯል፤ በርካታ ዜጎችም ከኖሩበት ጎስቋላ ኑሮ እንዲላቀቁ በር ከፍቷል፡፡ ይህ ከተማዋን በእጅጉ እያዘመነና ለነዋሪዎቿ ኑሮ ምቹ እንድትሆን እያደረገ ያለው የመጀመሪያ ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት በመጠናቀቅ ላይ ሲሆን፣ በቅርቡም ሁለተኛው ምዕራፍ በይፋ መጀመሩ ይታወቃል፡፡

የዝግጅት ክፍላችንም ቅኝት ባደረገበት ወቅት በኮሪደር ልማቱ ምክንያት ለተነሱ ነዋሪዎቹ የተሰጡት ምትክ ቤቶች በውበታቸው፣ በጥራታቸው፣ በንፅህናቸው እንዲሁም በስፋታቸው የሚመሰገኑ ሆነው አግኝቷቸዋል። ከነዋሪዎቹም እንደተረዳነው በእነዚህ አይነት ቤቶች አዲስ ዓመትን መቀበልና ማክበር ልዩ ስሜትን የሚሰጥ ነው። ዓመቱን በመልካም ስሜት እንዲጀምሩ ትልቅ ተስፋና መነሳሳት የሚፈጥር ነው፡፡ በመጨረሻም ለመላው ኢትዮጵያውያን መልካም አዲስ ዓመት ተመኝቷል፡፡

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review