ቺሊ ኢትዮጵያን ከሁለትዮሽ ግንኙነት ባሻገር በአፍሪካ ለምታደርገው እንቅስቃሴ ቁልፍ አጋር ማድረግ እንደምትፈልግ ገለጸች

You are currently viewing ቺሊ ኢትዮጵያን ከሁለትዮሽ ግንኙነት ባሻገር በአፍሪካ ለምታደርገው እንቅስቃሴ ቁልፍ አጋር ማድረግ እንደምትፈልግ ገለጸች

AMN – ጥቅምት 29/2017 ዓ.ም

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኢትዮጵያ ጉብኝት ካደረጉት የቺሊ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግሎሪያ ዴ ለ ፎንቴ ጎንዛሌዝ ጋር ተወያይተዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ዘርፍ እየተመዘገበ ባለው ፈጣን ዕድገት እና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ ለምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ቀጣናዊ እና አካባቢው ባለው የሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያም ገለጻ አድርገዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትኩረት ከሰጣቸው መካከል የግብርና እና የማዕድን ዘርፎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቺሊ በእነዚህ ዘርፎች ታዋቂ በመሆኗ ኢትዮጵያ ተሞክሮ ለመቅሰም የቴክኒክ ትብብር ማግኘት እንድትችል እና የቺሊ ባለሀብቶች በእነዚህ መስኮች በኢትዮጵያ እንዲሰማሩ አምባሳደር ምስጋኑ ጥሪ አቅርበዋል።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ የቺሊ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ቡድን በኢትዮጵያ ጉብኝት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የቺሊ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግሎሪያ ዴ ለ ፎንቴ ጎንዛሌዝ በበኩላቸው አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር እንደምትፈልግ አረጋግጠዋል።

ክብርት ግሎሪያ ጎንዛሌዝ ቺሊ ኢትዮጵያን ከሁለትዮሽ ግንኙነት ባሻገር በአፍሪካ ለምታደርገው እንቅስቃሴ ቁልፍ አጋር ማድረግ ትሻለች ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ምክትል ሚኒስትሯ ባለፈው ዓመት የተካሄደው የሁለትዮሽ የፖለቲካ ምክክር ግንኙነቱ በብዙ ዘርፎች ላይ እንዲያተኩር ቁልፍ ሚና መጫወቱን አስታውሰዋል።

ሁለቱ ወገኖች ኢትዮጵያ እና ቺሊ በደቡብ ደቡብ ትብብር የበለጠ በጋራ ተቀራርበው በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያም መክረዋል።

ሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 80ኛ ዓመት በቀጣይ ዓመት በጋራ ለማክበር ዝግጅት ለማድረግም ተስማምተዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review