አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራን ለማሳለጥ ለዲጂታል አሰራሮች ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል

AMN – ጥቅምት 29/2017 ዓ.ም

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራን ለማሳለጥ ለዲጂታል አሰራሮች ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ተጠቆመ።

በቻይና አውሮፓ ዓለም አቀፍ ቢዝነስ ትምህርት ቤት የአፍሪካ ካምፓስ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ማቲው ሳሚኒይ እንዳሉት የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ ለሚተገበሩ መርሃ ግብሮች ቴክኖሎጂ ወሳኝ ሚና አለው።

አፍሪካ የንግድና ምጣኔ ሃብት ትስስር በማጠናከር ብልጽግናን እውን ለማድረግ ተግባራዊ ካደረገቻቸው መርሃ ግብሮች መካከል የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና አንደኛው መሆኑን አስታውሰዋል።

በአህጉሪቱ በሚኖረው 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ህዝብ መካከል የሚደረገውን የንግድ ስርአት በማጠናከር አንድነቷ የተጠናከረና የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ ስርዓቱን በቁርጠኝነት መተግበር ተገቢ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የኤሌክትሮኒክስ ግብይትን ማስፋፋት፣ የዲጂታል መረጃ አያያዝና ልውውጥን ማጠናከር እንዲሁም በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን መተግበር አስፈላጊ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማትን ማስፋፋት፣ የህግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት፣ ትብብርን ማጠናከር እንዲሁም ዘርፉን ለውድድር ክፍት ማድረግ በትኩረት መሰራት ካለባቸው ተግባራት ውስጥ ጠቅሰዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ መሰረት ልማትን በማስፋፋት፣ ክህሎትን ለማዳበርና ፈጠራን ለማበረታታት እያከናወነች ያለው ተግባር የሚበረታታ እንደሆነ አንስተዋል።

በአህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናው ሁሉንም ተጠቃሚ ለማድረግ የወጣቶችና ሴቶችን አቅም በዲጂታል ቴክኖሎጂ ማብቃት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

አፍሪካ በዓለም አቀፍ እንዲሁም በአህጉር ደረጃ ትብብርን በማጠናከር በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለውን ሰፊ የስራ እድል መጠቀም እንደሚገባት አመላክተዋል።

ለዚህም ወጣቱን በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ሊያደርጉ የሚችሉ ትምህርትና ስልጠና ላይ ትኩረት ማድረግ ተገቢ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ የጀመረችው የዲጂታል ጉዞ ሌሎች ሀገራትም በመጋራት ለጋራ እድገት በጋራ መስራት አለባቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review