AMN – መስከረም 14/2017 ዓ.ም
በኒውዮርክ እየተካሄደ ከሚገኘው 79ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (የ.ተ.መ.ድ. ) ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዩ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ አምባሳደር ታዬ በቅርቡ በቻይና በተካሄደው 4ኛው የቻይና አፍሪካ መድረክ (ፎካክ) የመሪዎች ጉባዔ ወቅት ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩ በርካታ ስምምነቶች መፈራረማቸው አገራቱ ለግንኙነታቸው የሚሠጡት የላቀ ትኩረት አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ የፎካክ ጉባዔ የአፍሪካ ብሎም የኢትዮ -ቻይና ስትራቴጂካዊ አጋርነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ መሆኑን አውስተዋል ።
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዩ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር የምትጫወተውን ቁልፍ ሚና አድንቀዋል።
ሚኒስትሩ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውም “የምንግዜም ስትራቴጂክ አጋርነት” ( All Weather Stratagic Partnetship) መሆኑ በቀጣይ በርካታ ሥሪዎች በጋራ ለመስራት መሠረት የጣለ መሆኑን ገልፀዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቻይና ጉብኝት ወቅት ስምምነት የተደረሰባቸው የኢኮኖሚ ትብብር ኘሮጀክቶች እንዲሁም ከቀረጥና ታሪፍ ነፃ የገበያ ዕድሎች ትኩረት ተሠጥቷቸው ተግባራዊ እንደሚደረጉ አስታውቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ የአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ ሠላምና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ገለጻ ሠጥተዋል።
ሁለቱ ሚኒስትሮች ብሪክስን ጨምሮ በተለያዩ ዓለምአቀፍ መድረኮች ላይ በጋራ መስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ዙሪያ ሀሳብ መለዋወጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።