በዓለም አቀፍ ደረጃ የዲጂታል ክህሎት በዲጂታል የታገዘ ማህበረሰብ ፈጥሯል፡፡ በዚያው ልክ አዳዲስ የስራ እድሎችን “እንካችሁ” እያለ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ግን በዚህ ዘርፍ በበቂ ደረጃ እየተወዳደረች ነው ማለት የሚቻል አይመስልም፡፡ ወደ ኋላ ቀርታለች ቢባልም ማጋነን አይሆንም፡፡ ታድያ ትውልዱን በፍጥነት የዲጂታል ክህሎት ማስታጠቅ ካልተቻለ ዘመኑን የሚመጥን ተወዳዳሪ ዜጋም ይሁን ሀገር መፍጠር አዳጋች እንደሚሆን እሙን እየሆነ መጥቷል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን አሁን ለዘርፉ ትኩረት እየሰጠች ትገኛለች፡፡ በዲጂታል ክህሎት ያለባትን ክፍተት ለመሙላት የመሰረታዊ የኮምፒውተር እውቀት እና ሁለንተናዊ የዲጂታል ክህሎት መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ ለሀገሪቱ ወጣቶች ተደራሽ ለማድረግ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። የሀገር ተስፋ የሚሆኑ 5 ሚሊዮን ኮደሮችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማፍራትና ብቁ ለማድረግ እየተሰራ ያለው ስራ የዚህ ጥረት አንዱ ማሳያ ነው ሊባል ይችላል፡፡
አምስት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች መርሃ ግብር በኢትዮጵያ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግስታት መካከል በተደረገ ስምምነት የተነደፈ የዲጂታል ክህሎት ስልጠና መርሃ ግብር ነው፡፡ ዓላማውም ወጣቱ ትውልድ በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ መሳተፍ የሚያስችለው የዲጂታል ክህሎት እንዲኖረው ማስቻል ነው።
መርሃ ግብሩ ለሁሉም ተደራሽ የሆኑ የኦንላይን ኮርሶችን እና ሌሎች ደጋፊ አገልግሎቶችን በማቅረብ እ.አ.አ በ2026 አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን በፕሮግራሚንግ፣ በዳታ ሳይንስ እና አንድሮይድ ልማት መሰረታዊ የዲጂታል ክህሎት ማስታጠቅን ግብ ያደረገ ነው። ወጣቶቹ በመርሃ ግብሩ በመሳተፍ በግላቸው የሚያገኙት ጥቅም እንዳለ ሆኖ የመርሃ ግብሩ ውጤታማነት ለዲጂታል ኢትዮጵያ ስኬት እና ተወዳዳሪነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
የስልጠናዎቹ ይዘቶች የሚቀርቡት ዓለም ዓቀፍ በሆነው የዲጂታል ክህሎቶችን በኦን ላይን በማስተማር ስመጥር በሆነው ከዩዳሲቲ ፕላትፎርም ጋር በመተባበር ነው፡፡ አንዱ ኮርስ እስከ 6 ሳምንታት ሊወስድ እንደሚችልም ተገልጿል፡፡
አምስት ሚሊዮን ኮደሮችን ለመፍጠር ተወጥኖ እየተተገበረ በሚገኘው መርሃ ግብር ተካፋይ የሆኑ ሰልጣኞች ለዝግጅት ክፍላችን ባጋሩት ሀሳብ የዲጂታላይዜሽኑን ዓለም ለመቀላቀልና ተወዳዳሪ ለመሆን ቀላል የማይባል ክህሎት እየቀሰሙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሀሳባቸውን ካጋሩን መካከል አንዱ የሆነው ተማሪ ሶፎንያስ ወዳጄ የ2010 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈትኖ ውጤት እየጠበቀ ይገኛል፡፡ በፕሮግራሚንግ ፈንዳሜንታልስ (Programming Fundamentals) የ6 ሳምንታት ኮርሶችን ወስዶ በማጠናቀቅ ሰርተፊኬቱን መቀበሉን ነግሮናል፡፡
የኮደሮችን ዓለም እንደተቀላቀለ ስልጠናውን አሃዱ ብሎ የጀመረበትን የፕሮግራሚንግ ፈንዳሜንታልስ ኮርስ በተሰጠው የጊዜ ገደብ አጠናቅቆ ፈተና በመውሰድ አሁን ላይ ሰርተፊኬቱን ተቀብሏል፡፡ ተማሪ ሶፎንያስ ይህንን ኮርስ በመውሰዱ ከዚህ ቀደም በጉዳዩ ላይ ከነበረው መረዳት ጋር ተዳምሮ የተሻለ ዕወቀት እንዳገኘበት ተናግሯል። ይህን ስልጠና ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ሁለተኛው ስልጠና መሸጋገሩንም ገልፆልናል፡፡
ተማሪ ሶፎንያስ አሁን የአንድሮይድ ደቨሎፐር ፈንዳሜንታልስ (Android Developer Fundamentals) ስልጠና ጀምሯል፡፡ እስከ አሁን ያለው ሁኔታ በጣም ጥሩ እንደሆነና በቀጣይ ኮርስ በጥሩ ሁኔታ ለማጠናቀቅ እየሰራ መሆኑን ጠቁሞ፣ ይህ ስልጠና በዚህ ሰዓት መምጣቱ መልካም ዕድል እንደሆነና የዕረፍት ጊዜውንም በአልባሌ ቦታ ከማሳለፍ እንደታደገው ተናግሯል፡፡
ተማሪ ሶፎንያስ በቀጣይ የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት ለመከታተል ዕቅድ አለው፡፡ አሁን እየወሰዳቸው ያሉ ኮርሶች ለሚያልመው የአይ.ሲ.ቲ ባለሙያ የመሆን ውጥን ሁነኛ መንደርደሪያ እንደሚሆንለትና በ2017 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲ ሲገባ እንደሚጠቅመው ይናገራል፡፡ ለቀጣይ ህይወቱም ትልቅ ትርጉም እንዳለው ተናግሯል፡፡ በዚህ ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች የእድሉ ተጠቃሚ ቢሆኑ ለነገ ህይወታቸው ጠቃሚ መሆኑን ተማሪ ሶፎንያስ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
ተማሪ ሶፎንያስ እንደሚለው ወቅቱ ወደ ዲጂታላይዜሽን እየተለወጠ በመሆኑ በሁሉም ረገድ ተወዳዳሪ ለመሆን ይህን በነጻ የተገኘውን ዕድል በመጠቀም ሁሉንም ኮርሶች በመውሰድ በዘርፉ ውጤታማ የመሆን ፍላጎት አለው፡፡
ሌላው ሰልጣኝ ቃልአብ ነጋ ይባላል፡፡ ይህን ዕድል በዓመቱ መጨረሻ ላይ ማግኘቱና በአዲሱ ዓመት በቴክኖሎጂ ዘርፍ አዲስ ዕቅድ እንዲያወጣ እንዳደረገው ይናገራል፡፡ ቃልአብ (Programming Fundamentals እና Android Developer Fundamentals) ተምሮ ጨርሶ ሰርተፊኬትም አግኝቷል። አሁን የመጨረሻውን (Data Science Fundamentals) ኮርስ እየወሰደ ይገኛል፡፡ ሥልጠናው ወደፊት የሚያስበውን ለማሳካት የሚያስችለውን ክህሎት በቀላሉ ለመረዳት የሚያስችል መሆኑን ቃልአብ ገልጿል። የዚህ ክህሎት ባለሙያ መሆን ተወዳዳሪነትን የሚጨምርና ተፈላጊነትን የሚያሳድግ በመሆኑ በተገኘው ዕድል ደስተኛ መሆኑን ጠቁሟል።
“ስልጠናው በኦንላይን በመሆኑ በፈለግኩበት ጊዜ ለመሰልጠን አስችሎኛል” የሚለው ቃልአብ የጊዜ ጥያቄ ሳይኖርበት በየትኛውም ሰዓትና ቦታ ሆኖ የእጅ ስልኩን ተጠቅሞ ስልጠናውን መከታተል መቻሉን ተናግሯል፡፡
ወጣቱ እንደገለጸው፣ ይህ ለወጣቶችም ለሀገርም ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም ሰው ተምሮ ሲጨርስ ህጋዊ ሰርተፊኬት ያገኛል፡፡ ይህ ደግሞ ዓለም ዓቀፍ ተወዳዳሪ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም በየትኛውም አካባቢ ያሉ ወጣቶች በዚህ የሙያ ዘርፍ ተወዳዳሪ ብሎም ተጠቃሚ ለመሆን ተመዝግበው መማር እንዳለባቸው መክሯል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ስማርት ሲቲ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ቱሉ ጥላሁን (ዶ/ር)፣ ወጣቶችን በኢትዮ-ኮደርስ ተጠቃሚ ለማድረግ ብርቱ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፣ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ 300 ሺህ ወጣቶች የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን፣ ፕሮግራሙ ይፋ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ከ42 ሺህ በላይ ወጣቶች ተመዝግበው ስልጠናውን እየተከታተሉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በየበጀት ዓመቱ 75 ሺህ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ይህን ስልጠና እንዲወስዱ ታስቦ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ ወጣቶቹ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተለያዩ አይነት መንገዶች ቅስቀሳ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
እንደ የምክትል ቢሮ ኃላፊው ማብራሪያ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የተሻለ የቴክኖሎጂ ክህሎት ያላቸው ግለሰቦች እንደመኖራቸው መጠን በዚህ ስልጠና ውጤታማ የመሆን ዕድል አለ፡፡ ሰልጣኞቹ ሰርተፊኬት የማግኘት ዕድል ስላላቸው ዓለም አቀፍ ገበያው ላይ እንዲሳተፉ በር ይከፍትላቸዋል፡፡
በርካታ ወጣቶች የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቢሮው ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር ውይይት ስለማድረጉና በዕረፍት ላይ ያሉ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ሲመለሱ የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዩኒቨርሲቲው ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርግ መግባባት ላይ መደረሱንም ቱሉ (ዶ/ር) ገልፀዋል፡፡
ይህ ስራ ውጤታማ እንዲሆን ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከአዲስ አበባ ስራ እና ክህሎት ቢሮ፤ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ እና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው፡፡ ሁሉ የድርሻቸውን እንዲወጡ የጋራ አቅጣጫ መያዙንም ቱሉ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በክረምቱ ወቅት ስልጠና ላይ የቆዩት መምህራን በስልጠናው የመዝጊያ መርሃ ግብር ላይ በኢትዮ ኮደርስ መርሃ ግብር ዙሪያ ትልቅ የግንዛቤ መፍጠሪያ ስራ ተሰርቷል የሚሉት ቱሉ (ዶ/ር)፣ ይህም በቀጣይ በየትምህርት ቤታቸው የስልጠናውን አስፈላጊነት እስከታች እንዲያወርዱ እንደሚረዳቸው ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮ ኮደርስ መርሃ ግብር የተመዘገበ ሁሉ ኮርሶቹን ጨርሶ የሰርተፊኬት ባለቤት እንዲሆን ነው የሚጠበቀው ያሉት ቱሉ (ዶ/ር)፣ ሰልጣኞች በሚያጋጥሟቸው አንዳንድ ችግሮች ወደ ኋላ እንዳይመለሱ ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ይገኛል። ከሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች መካከል የኮምፒውተር እና የኢንተርኔት ችግሮች ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህን ችግሮች ለማቃለል በከተማዋ የሚገኙ የትምህርት ተቋማት በተለይም ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸው የሚጠቀሙበትን የአይ.ሲ.ቲ ላቦራቶሪዎች ለተቋሞቻቸው ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ደህንነቱ ተጠብቆ ለወጣቶችና ለአካባቢው ማህበረሰብም አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ሰልጣኞቹ ለስልጠናው የሚያስፈልጉ መማሪያ ሞጁሎችና ቪዲዮዎችን ከኦን ላይን በማውረድ በእጅ ስልካቸው ኦፍ ላይን ላይ ሆነው የሚሰጡ መልመጃዎችን በመስራት ለሰርተፊኬት ብቁ የሚያደርገውን ፈተና ብቻ ኦን ላይን ሆኖ መውሰድ እንደሚቻል ቱሉ (ዶ/ር) ተናግረዋል። ይህ ዕድል በከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት እንዲሁም በኢትዮጵያና በተባበሩት አረብ ኤሚሬት የሀገር መሪዎች የጠበቀ ወዳጅነት የተገኘ ሲሆን፣ አንዱን ኮርስ ብቻ ሰልጥኖ ሰርተፊኬት ለማግኘት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነው፡፡ ስለሆነም የተገኘው ዕድል በጣም ትልቅ ስለሆነ ፍላጎት ያለው ማንኛውም ሰው ተመዝግቦ መሰልጠን ይችላል፡፡ የመርሃ ግብሩ ሂደት በየሳምንቱ ሐሙስ ቀን በጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት በተቋቋመው ኮሚቴ ይገመገማል፡፡
ቢሮው ይህንን ስራ ለማሳለጥ ብሎም ሰልጣኞች ችግር ሲገጥማቸው እርስ በርሳቸው እንዲደጋገፉ የቴሌግራም ቻናል በመክፈት በሚያጋጥማቸው ችግር ውይይት እንዲያደርጉ መድረክ አመቻችቷል፡፡ በመድረኩ ላይ በርካታ ወጣቶች አባል ሆነዋል፡፡
ይህ ግንዛቤ ከዚህ በፊት አልነበረም የሚሉት ቱሉ (ዶ/ር) የቴሌግራም ፕላትፎርሙ እነዚህንና ሌሎች ተግዳሮቶችን እርስ በእርሳቸው መፍትሄ እንዲሰጣጡ እያደረገ ይገኛል ብለው፣ የኮምፒውተር እጥረቶችን ለማቃለል በየወረዳው ላሉ የወጣቶች ማዕከላት አስፈላጊ የሆኑ ቁሶች እንዲሟሉ የማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ሲሉም አክለዋል፡፡
ወጣቶቹ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ራሳቸውን ወደሚፈልጉበት የዕድገት ደረጃ ከፍ ለማድረግ የሚያግዟቸውን ክህሎቶች ከሥልጠናው እያገኙ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡ ስልጠናው ለእንደ ቃልአብና ሶፎኒያስ ያሉ ወጣቶች አዲሱን ዓመት በአዲስ መንፈስ፣ እውቀትና ክህሎት የመቀበል ዕድል እንደፈጠረላቸው ይናገራሉ፡፡
በቶለሳ መብራቴ