AMN-መስከረም 21/2017 ዓ.ም
ከአዲስአበባ ፣ ከአማራ፣ ከኦሮሚያ፣ ከጋምቤላ፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ከአፋር ክልሎች ለተውጣጡ ከ200 በላይ ለሚሆኑ በመሬትና ካዳስተር እንዲሁም በከተማ ገቢ ሪፎርም ዘርፍ ለተሰማሩ አመራሮችና ባለሙያዎች በተለያዩ የከተማ መሬት የሕግ ማዕቀፎች ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሠጠ ነው፡፡
ስልጠናውን በይፋ ያስጀመሩት የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የመሬትና ካዳስተር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ብዙዓለም አድማሱ እንደተናገሩት የከተማ መሬትና መሬት ነክ ሀብትን በካዳስተር ሥርአት መዝግቦና ቆጥሮ በመያዝ የመንግስትና የህዝብን ጥቅም ማረጋገጥ እንደሚገባ ጠቅሰው በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ባለሙያዎች ከሚኒስቴር መ/ቤቱ የሚወርዱት የህግ ማዕቀፎች በአግባቡ ተግባራዊ መደረግ እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡
አቶ ብዙዓለም አክለውም ህገ-ወጥ የመሬት ወረራና በአቋራጭ ለመበልጸግ የሚሯሯጡ ዜጎችን ህጋዊ መስመርን ተከትለው እንዲሠሩ ማድረግ የሚቻለው ድጅታል አሠራርን ተግባራዊ በማድረግ በጥራትና በፍጥነት የከተማ መሬትን መዝግቦ በመያዝ ነው ብለዋል፡፡
ይህም እውን መሆን የሚችለው የስልጠናው ተሳታፊዎች ልምድና ተሞክሮአቸውን በአግባቡ ሥራ ላይ በማዋል የዘርፉን ፖሊሲዎችና አዋጆችን በትክክል መፈጸም ሲችሉ ነው ብለዋል ኃላፊው፡፡
በስልጠናው የመሬት አቅርቦት ማስተላለፍ እና ይዞታ አስተዳደር ነባራዊ ሁኔታ፣ የተሻሻለው የካሳ አዋጅ፣ የልማት ተነሺዎች መልሶ ማቋቋም የአሰራር ስርዓት፣ የመሬትና መሬት ነክ መረጃ አደረጃጀትና ተግዳሮቶች፣ የከተማ መሬት ምዝገባና የአመራሩ ሚና ምን መምሰል እንዳለበት በተለያዩ ባለሙያዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በቀጣይ ቀናትም የከተማ መሬት ይዞታ ወሰን ማካለል እና የቅየሳ አሰራር ሂደት፣ የከተማ ካዳስተር የካርታ ዝግጅት፣ የአድራሻ ሥርዓት ዝርጋታ አተገባበር፣ አዲሱ የፕሮፐርቲ ታክስ አዋጅ ዋና ዋና ነጥቦች እንደሚቀርቡ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡