አዲስ አበባ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ውብ ገጽታ እየተላበሰች ነው፡፡ ጎዳናዎቿ ሰፍተው፤ በውብ መብራቶችም ተሽቆጥቁጠው፡፡ አረንጓዴ መልበስ ብቻም ሳይሆን በፏፏቴዎች ውበትም እየፈኩ ነው፡፡ ልክ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ፊልሞችና የሙዚቃ ክሊፖች ላይ አይተን ስንደነቅባቸው እንደነበሩት የዓለማችን ምርጥ ከተማዎች ሁሉ አዲስ አበባም የእነዚህን ከተሞች ፈለግ እየተከተለች ነው ያስብላል፡፡
ይሄ የማዘመን ጉዞ ደግሞ አሁን ላይ አዲስ አበባ ለጉብኝትና ለመዝናናት የምትመረጥ ከተማ ጭምር እያደረጋት ይገኛል፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት እየሆነ ያለው የኮሪደር ልማት ነው፡፡ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት እየሆነ ያለው ይህ ልማት ለጎብኚዎችና ለአዲስ አበባ ነዋሪዎችም ጥሩ የመዝናኛ አማራጭ መሆኑን በሚገባ እየተመለከትን እንገኛለን፡፡ የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍልም በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የከተማዋ የውበት ማሳያ እየሆኑ ያሉ አዳዲስ የኮሪደር ልማት ስፍራዎችን ቃኝቷል፡፡ በዚህ ቅኝትም ይህ ልማት ለመዝናኛነት ምን ያህል እየተመረጡ ነው? የሚለውን ሊያስቃኛችሁ ወድዷል፡፡
አሁን ላይ በለውጥ ሂደት ላይ ያለችው አዲስ አበባ በርካታ ውብ እሴቶችና ቅርሶች በውስጧ ብትይዝም፣ የዚያን ያህል ደግሞ ውስጣዊ እንከኖችም ነበሯት፡፡ ጎዳናዎቿ ምቹነት አልነበራቸውም፡፡ የአይን ማረፊያ የሚሆኑ ስፍራዎች ፈልጎ ማግኘት ብርቅ ነበር። የመዝናኛ ስፍራዎቿ ይበልጥ ከመብልና ከመጠጥ ጋር የተቆራኙ ነበሩ፡፡ ‘እስኪ በእግሬ ልንሸራሸር’ ብሎ በአጋጣሚ ለወጣ ሰው ብዙም የሚመቹ አልነበሩም፡፡ እነዚህንና ሌሎች የአዲስ አበባን እንከኖች መዲናዋ የዕድሜዋን ያህል አለመዘመኗና ዕድገት አለማሳየቷ መገለጫ አድርገን ልንመለከታቸው እንችላለን፡፡
ይህንን የመዲናዋን እንከን ቁልጭ አድርጎ የሚያነሳልኝ አንድ ግጥም ልጥቀስ፡፡ ግጥሙ የተጻፈው በ1989 ዓ.ም ነው፡፡ ገጣሚው ደግሞ እውቁ የስነ ጽሁፍ ምሁር ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ነው። ገጣሚው “አዲሳባ” በተሰኘው ግጥሙ የአዲስ አበባን ከተሜነት ኪናዊ በሆነ አኳኋን ያጠይቃል። የከተሜነት ትርጉሙ ግር ቢለው አዲስ አበባን እንዲህ ሲል በሂስ ሸንቆጥ አድርጓታል፤
በመንገድሽ ስሄድ እየሄድኩ አልሄድም፣
ሱቅና ኪዮክስሽ፣ ለዓይን ማረፊያ አይተዉም፤
ጥርስ አንገት ማከሚያሽ፣
ዘፈን መነገጃሽ፣
መድሃኒት መሸጫሽ፣
ፎቶ ግራፍ ማንሻሽ፣
ለአቀማመጣቸው፣
ሥርዓትም የላቸው፡፡…
ገጣሚው በዚህ ግጥሙ የአዲስ አበባን ጉድፍ ነቅሶ በማውጣት ለመሄስ ሞክሯል፡፡ ዛሬ ላይ የአዲስ አበባን ክፍተቶች ለመድፈን እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ለገጣሚው ምክንያታዊ ሂስ ምላሽ እየተሰጠ ይመስላል፡፡ ከእነዚህ ስራዎች መካከል አንዱ የመዲናዋን ውበት የሚጨምሩ ስራዎች ናቸው፡፡ ጉዳናዎቿን የማስፋት፤ ለዓይን ማራኪ እና አረንጓዴ ብሎም በእግር መንሸራሸርና አረፍ ብሎ መጨዋወት ለሚወዱ ሰዎች የሚሆኑ ስፍራዎች በመሰራት ላይ ናቸው፡፡ እነዚህ የኮሪደር ልማቱ አንድ አካል ናቸው፡፡
ሌላው የአዲስ አበባ ውበትና መዝናኛ እየሆኑ ካሉ አዳዲስ ፕሮጀክቶች መካከል፣ ፒያሳ ላይ የተሰራው የዓድዋ ድል መታሰቢያ እና ፊት ለፊት (ማለትም አራዳ ህንጻ አካባቢ)፣ ከፒያሳ አራት ኪሎ፣ መስቀል አደባባይ፣ የወዳጅነት ፓርክ፣ የእንጦጦ ፓርክ፣ አብርሆት ቤተ መጻህፍትና ዙሪያውን መጥቀስ ይቻላል። እነዚህን አካባቢዎች ከዚህ ቀደም በተለየ በብዙ ሰዎች የሚጎበኙና የሚዘወተሩ የመዝናኛ አማራጮች እየሆኑ ናቸው፡፡
እኔም የፒያሳ አድባር ተደርገው ከሚታዩ ቤቶች መካከል አንዱ በሆነው ቼንትሮ ካፌ ደጃፍ ላይ ማኪያቶ አዝዤ ዙርያዬን እየቃኘሁ ነው። ከፊት ለፊቴ የፒያሳ ጥንታዊ ኪነ ህንጻዎችና ምልክት የሆኑት ሲኒማ ኢትዮጵያና ትሪያኖን እያየሁ የፒያሳን ትናንት እና ዛሬ በአዕምሮዬ አውጠነጥናለሁ፡፡ ሁለቱም ቤቶች ውበት ጨምረው ፒያሳን ሊያደምቋት እየተሞሸሩ ናቸው፤ ማለትም እድሳታቸው እየተጠናቀቀ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ላይም ሆኖ ግን ሁለቱ የፒያሳ አድባሮች አምሮባቸዋል፡፡ እነዚህን ጥንታዊ ኪነ ህንጻዎች አተኩሮ ለተመለከታቸው ፊት ለፊታቸው ያለው የዓድዋ ድል መታሰቢያ እያዩ የተገረሙ ይመስላሉ፡፡ ምክንያቱም ያ ቦታ ለዓመታት ታጥሮ የነበረና ዙሪያውም በታክሲ እና በአውቶብሶች ሰልፍ የሚጨናነቅ ቦታ ነበር፡፡
ማኪያቶዬን ፉት እያልኩ ቼንትሮ በረንዳ ላይ ካጠገቤ ወንበር ከተጋሩኝ ጓደኛሞች መካከል ራሴን አስተዋውቄ መጨዋወት ጀመርን፡፡ በጨዋታችን መሃል ከፊቱ ፈገግታ የማይለየው ወጣት በረከት ተስፋሁንን ስለ ፒያሳ አሁናዊ ሁኔታዋ እንዲያወጋኝ ጠየቅሁት፡፡ እሱም እንዲህ ሲል መለሰልኝ፤ ፒያሳ በሌላ ውበትና መልክ በአዲስ ገጽ ተከስታለች፡፡ ከዚህ ቀደም በግርግርና በሁካታ እናውቃቸው የነበሩ ስፍራዎች በቦታቸው ዘመን ተሻጋሪ የዓድዋ መታሰቢያ መገንባቱ በጣም አስደሳች ነው፡፡ በፊት ቸርችል ቪው ተብሎ ይጠራ በነበረው ስፍራ ለአይን ሳቢ የሆኑ ፏፏቴዎች፣ አበባዎችና እነሱን ለማየት የሚያስችሉ ማረፊያዎች በዚህ አጭር ጊዜ መሰራቱ እንዳስገረመው ወጣቱ አጫውቶኛል፡፡
የዓድዋ ድል መታሰቢያ መግቢያ አካባቢ ብዙ ጎብኚዎች የሚጎበኙትና ለመዝናናት የሚመርጡት ስፍራ መሆኑን ለመመልከት ችያለሁ፡፡ በአካባቢው ህጻናት ወዲህና ወዲያ እያሉ ሲጫወቱ፣ አዋቂዎች በተሰሩ ማረፊያ ቦታዎች አረፍ ብለው ሲያወጉ፣ ብዙዎች ደግሞ በአካባቢው በተሰሩ ማራኪ ኪነ ህንጻዎችና የመዝናኛ ስፍራዎች እየታከኩ ፎቶ ሲነሱ ይታያሉ፡፡ ይሄ ደግሞ መዲናዋ ሌላ ተጨማሪ የአይን ማረፊያና የመዝናኛ አማራጭ እያገኘች ለመሆኗ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡
በረከትም ስለ ፒያሳ ካወጋኝ ነገሮች መካከል አንዱ ተጨማሪና በአይነታቸው የተለዩ የመዝናኛ አማራጮች ፒያሳ እንዳገኘች ነው። ከዚህ ቀደም ፒያሳ በኬክ ቤቶች፣ በሲኒማ አፍቃሪዎች፣ በውብ ካፌዎች፣ በታሪካዊ ኪነ ህንጻዎችና ከሁሉም በላይ ደግሞ በምሽት መዝናኛ ክለቦቿ ነበር ይበልጥ የምናውቃት። አሁን ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ግን ፒያሳም ሆነች አዲስ አበባ ተጨማሪና የተለያዩ ሰዎችን ያማከሉ የመዝናኛ አማራጮች እንደሚያስፈልጓት ያሳዩ ናቸው ሲል አጫውቶናል፡፡
ከቼንትሮ ወጥቼ ቀኜን ይዤ መራመድ ጀመርኩ፡፡ ወደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ መግቢያ አካባቢ ቀጥታ አመራሁ፡፡ በመግቢያው አካባቢ ባሉ የመዝናኛ ስፍራዎች ከስምንት ዓመት ሴት ልጇ ጋር ስትዝናና ያገኘኋት ወይዘሮ ሰናይት ለይኩን ስለ ፒያሳ ትንሽ እንድታወጋኝ ጠየቅኋት። ልጇን በእጅ ስልኳ ፎቶ አንስታ ስታበቃ እንዲህ አለችኝ፤ ከዚህ ቀደም ፒያሳ ህጻናትና ልጆችን ለማዝናናት ብዙም የምትመረጥ አካባቢ አልነበረችም፡፡ ግፋ ቢል ልጆችን ባቅላባና ኬክ ለመጋበዝ ካልሆነ በስተቀር አሁን እየታዩ ያሉ የመዝናኛ አማራጮች እንዳልነበሯት አወጋችኝ። በአካባቢው ውሃ እየተራጩ ወዲህና ወዲያ የሚሯሯጡትን ልጆች በጣቷ እየጠቆመችኝ፤ “ይሄ ነገር ቀላል አይደለም፡፡ ልጆች በዚህ ልክ መደሰታቸውና ለአይናቸው የሚማርክ ነገር ማየታቸው ትልቅ ነገር ነው” ስትል አዲስ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ለልጆች ጭምር ጥሩ የመዝናኛ አማራጭ እየሆኑ እንዳለ ተናግራለች፡፡
ሌላው ለመዲናዋ አዲስ እይታ ከፈጠሩ ስፍራዎች መካከል አንዱ አራት ኪሎ አካባቢ አንዱ ነው፡፡ ከአራት ኪሎ ወደ ፒያሳ የሚያስኬደው መንገድ አንድም ለመኪና ካልሆነ በስተቀር በእግሩ መንሸራሸር ለሚፈልግ ሰው ምቹ አልነበረም፡፡ በጎዳናዎቿ ግራና ቀኝም ይሄ ነው የሚባል ለአይን የሚማርክና አረፍ በማለት የሚታይ ነገር አልነበረም፡፡ የኮሪደር ልማቱ ከተጀመረ ከቅርብ ወራት በኋላ ግን የአራት ኪሎ መልክና ገጽ በጣም ተቀይሯል፡፡ ጎዳናዎቿ በጣም ሰፍቷል፡፡ ስፋታቸው በእግር ለመንሸራሸር ለሚወድ ሰው እጅግ የተመቸ ነው፡፡ በመንገድ ዳርና ዳር ላይ አረፍ ብሎ ለመጨዋወትና ለመዝናናት ለሚሻ ሰው የሚመቹ አረንጓዴ ስፍራዎች ተሰርተዋል፡፡ ከእነዚህ ውብ ቦታዎች መካከል አንዱ አራት ኪሎ ብርሃንና ሰላም ጎን የተሰራው ውብ ስፍራ ይገኝበታል፡፡
በዚህ አካባቢ ማረፊያ ወንበሮች፣ ማራኪ አበባዎች፣ እጅግ የሚያምር ትንሽዬ ፏፏቴ ተሰርቷል፡፡ ስፍራው ለአራት ኪሎ አዲስ እይታና ውበት ሰጥቷል፡፡ ሰዎችም በአካባቢው አረፍ ብለው ሲጨዋወቱ፣ ፎቶ ሲነሱና በተመስጦ ቁጭ ብለው የሚያስቡ ሰዎች መመልከት ይቻላል፡፡ እኔም በዚሁ አካባቢ በተሰራው አንድ ማረፊያ ወንበር ለብቻቸው ተቀምጠው ወዳየኋቸው አዛውንት አመራሁ፡፡ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ማውጋት ጀመርን፡፡ ስማቸው እንዳለ ፋንታሁን ይባላል፡፡ የጡረታ ጊዜ ላይ እንደሆኑ ያጫወቱኝ እኝህ አዛውንት፤ በመዲናዋ በአጭር ጊዜ እንዲህ አይነት ማራኪና አረፍ ብሎ ለመዝናናት ለሚሻ ሰው የሚሆኑ አማራጮች መሰራታቸው ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው፡፡ መሰል ስራዎች ለከተማዋ ገጽታም ላቅ ያለ አስተዋጽኦ አላቸው ሲሉ አቶ እንዳለ አጫውተውኛል፡፡
በሌሎች ሃገራት እንደሚታየው ውብ ከተሞች ለነዋሪዎችም ሆነ ለጎብኚዎች መዝናኛን በማቅረብ ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታሉ። ውብ ከተሞች ለመዝናኛ የሚያበረክቱት ጠቃሚ አስተዋፅዖ ከመላው ዓለም የሚመጡ ቱሪስቶችን የሚስቡ ድንቅ ምልክቶች እና መስህቦች በውስጣቸው መያዛቸው ብቻ አይደለም። ከዚያም ባሻገር፣ ውበት የተላበሱ ጎዳናዎች፣ ለአይን ማረፊያ የሚሆኑ ስፍራዎች፣ ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎትና ልዩ ልዩ የመዝናኛ አማራጮችም ጎብኚዎችን በመሳብ ረገድ ሚናቸው ትልቅ ነው፡፡ ገና ከአሁኑ አዲስ አበባ ውስጥ እየተሰሩ ያሉ የኮሪደር ልማቶች ለሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ለሚመጡ ጎብኚዎች ጥሩ የመዝናኛ አማራጭ እየሆኑ ናቸው፡፡ ይህንን አስተዋጽኦ በእነዚህ አካባቢዎች ዞር ዞር ብሎ ቅኝት በማድረግ በቀላሉ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
የአዲስ አበባን “አጠቃላይ የመንገድ ሽፋን እና ዘመናዊነት እንዲሁም የትራንስፖርት ፍሰት ወደ ላቀ ደረጃ ሊያሳድግ ይችላል” የተባለለት “የመንገድ ኮሪደር ልማት”፤ በከተማዋ ካቢኔ የጸደቀው የካቲት 15፤ 2016 ነበር። በዚህ ፕሮጀክት እንዲለሙ ዕቅድ የተያዘላቸው የመንገድ ኮሪደሮች፤ ዓለም አቀፍ “የስማርት ሲቲ” ስታንዳርድን በማሟላት የአዲስ አበባ ከተማን ደረጃ ከፍ ለማድረግ ታሳቢ ያደረጉ እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በአብርሃም ገብሬ