AMN – ሐምሌ 04/2016 ዓ.ም
“ኢትዮጵያን የምናጸናው በውትድርና ህይወታችንን ከፍለን ብቻ ሳይሆን መልክዓ ምድሯን በመጠበቅ ጭምር ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በጫካ ፕሮጀክት ስፍራ የአፕል ችግኞችን ተክለዋል፡፡
ይህንን አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ ፤ ዘንድሮ “የምትተክል ሀገር የሚያጸና ትውልድ” በሚል መሪ ቃል በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ንቅናቄ መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡
ለዚህም 8 ቢሊዮን ገደማ ችግኞች መፍላታቸውን እና የህብረተሰቡ መነቃቃት እና የመትከል ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዘንድሮ ከዚህ ቀደም ከሚደረገው የአተካከል ዘዬ በተወሰነ ደረጃ እንዲለወጥና እንዲሻሻል መታሰቡን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡
በተለይም በየአካባቢው ያለውን የአፈር መሸርሸር ለመታደግ የእርከን ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን በመግለጽ በዛሬው ዕለትም በጫካ ፕሮጀክት ስፍራ ከሀረር እና ከኮንሶ ሙያተኞችን በማምጣት እርከን በመስራት አፕል መተከሉን ተናግረዋል፡፡በዚህም አፈሩን መታደግ እና የሚበላ ነገር መትከል ተችሏል ነው ያሉት፡፡
ተራራው በእርከን መልክ ባይሰራ የሚተከሉ ችግኖች በቀላሉ አይበቅሉም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሌሎች ቦታዎችም ሀገር በቀል ችግኞች እንደሚተከሉ ገልጸዋል፡፡
ዛሬ የተሰራው ስራ ተራራውን መልሶ ምርታማ ለማድረግ የሚያስችል ስራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡ለዚህም የኮንሶና የሀረር አርሶ አደሮች እርከኑን በአጭር ቀናት ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡
ይህ ኢትዮጵያ ያላት ልምድና እውቀት በሀገር ደረጃ ሊስፋፋ እና ሊያድግ እንደሚገባውም ነው የጠቆሙት፡፡
እስካሁን የነበረው የመብቀል መጠን 80 በመቶ ገደማ እንደነበር በማስታወስ ይህንን ለማሻሻል ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ 2 በመቶ ብቻ የነበረው የአረንጓዴ ሽፋን አሁን ላይ 18 በመቶ ገደማ መድረሱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት 30 በመቶ ለማድረስ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም የከተማዋን ስታንዳርዱን የጠበቀ የከተማ ግንባታ እና የአረንጓዴ ከባቢ ስብጥር ማስተካከል እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
አዲስ አበባ በጥቂት ዓመታት ንጹህና አረንጓዴ ከተማ እንደምትሆንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አረጋግጠዋል፡፡
“ኢትዮጵያን የምናጸናው በውትድርና ህይወታችንን ከፍለን ብቻ ሳይሆን መልክዓ ምድሯን በመጠበቅ ጭምር ነውም” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ቦታዎች በእንክብካቤ ጉድለት መጥፋታቸውን በማንሳት ይህም ድርቅን ጨምሮ የተለያዩ ችግሮች ማስከተሉን ተናግረዋል፡፡
የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ በማከምና በማዳን ለትውልድ ማሸጋገር ይገባል ብለዋል፡፡
በሰፊና ሁሴን




