በሰው ልጆች የዕውቀት ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ አብዮትና አስተሳሰባዊ ለውጥ እንዲፈጠር ካደረጉ ዘርፎች መካከል ፍልስፍና ቀዳሚው ተጠቃሽ ነው፡፡ የሰው ልጅ አኗኗር፣ ባህል፣ አስተሳሰብ፣ ዓለምን የሚረዳበት አተያይ ምንነት ላይ ጥልቅ ጥያቄዎችን በማንሳት፣ በምክንያት በመሞገትና በመሄስ ረገድ የፍልስፍና ትምህርትና ፈላስፎችን ያህል የተጋ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ፈላስፎች ብዙሃኑ የተስማማበትና በባህል ውስጥ ጭምር ጸንቶ የኖረን ጉዳይ ሳይቀር በምክንያት በመሄስና ህጸጾችን ነቅሶ በማውጣት ለውጥ እንዲመጣ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል። በምክንያት የሚያስቡ ሰዎች በማህበረሰቡ ውስጥ እንዲበዙ፣ ለዘመናት በብዙዎች ዘንድ ስምምነት ያገኙ ዕሳቤዎችን ጭምር በጥንቃቄ እንዲመረምሩና ያመኑበትን ዕውነት እንዲኖሩት የፍልስፍና ትምህርት የማይተካ ሚና አለው፡፡
ፈላስፎች ፍልስፍናን በተለያዩ አውዶች ላይ ሆነው ይበይኑታል፡፡ ብዙዎችን ሊያስማማ የሚችል አንድ ጉዳይ ቢኖር፣ ፍልስፍና ያለመታከት ጥያቄዎችን መጠየቅ፣ ህይወትን ጭምር በምክንያት መሞገት፣ ማህበረሰብን ብቻ ሳይሆን የገዛ ራስን ጭምር መሄስና አዳዲስ ዕይታዎችን መፈንጠቅ የፍልስፍና አበይት መገለጫዎች ናቸው፡፡ በአጭሩ ፍልስፍና ጥበብን የመውደድ ዝንባሌ ሆኖ፤ ራስን፣ አካባቢን፣ የሚኖሩበትን ባህል፣ ዓለምን በጥልቀት ለመረዳት ጥረት ማድረግ ነው፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍም እኤአ ህዳር 22 (በትናንትናው ዕለት) የተከበረውን የዓለም የፍልስፍና ቀንን መነሻ በማድረግ ከሀገራችን ጥልቅ አሳብያን እና ፍልስፍናዊ ዕሳቤዎቻቸውን በወፍ በረር ልናስቃኛችሁ ወደድን።
ዘርዐ ያዕቆብ
በ16ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ተወልዶ በ17ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ የኖረው ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘርዐ ያዕቆብ ትልቅ የሃሳብ ገበሬ ነው፡፡ ስለ ህይወት፣ ስለ ሃገር፣ ስለ ማህበረሰብና ስለ ግለሰብ ጭምር ጥልቅ ጥያቄዎችን አንስቷል፡፡ ጥልቅ ሂሶችንም ሰንዝሯል፡፡ በራሱ የአስተሳሰብ ጉዞና ምርምር ታግዞ የጻፈው “ሐተታ ዘርዐ ያዕቆብ” የተሰኘ ሥራው ዘመን ተሻጋሪና ዛሬም ድረስ በአድናቆት የሚወሳ ስራው ነው፡፡
“ሐተታ ዘርዓ ያዕቆብ” የረቀቁና የጠለቁ ትንታኔዎችን ስለ ሰው ልጅ ተፈጥሮ ያነሳል፡፡ ለዘርዐ ያዕቆብ ፍልስፍና መሰረት የሆነው፤ “ማንነትን በበጎ ነገር ማጠር” በማለት የሚያቀነቅነው አስተሳሰብ ውስጥ የሚበቅሉ የሃሳብ ፍሬዎችን በዚህ መጽሐፉ ጎልቶ ይነበባል።
ዘርዐ ያዕቆብ በፍልስፍናው ተለምዷዊ አኗኗራችንን በመሄስ፤ ለሚኖርበት ማህበረሰብ እንግዳ ጥያቄዎችን በማንሳት ጭምር ምላሽ ይሰጣል፡፡ ሌላው የዘርዐ ያዕቆብ ፍልስፋና፤ ወሰን ያልተበጀለትና ሁሉን አቀፍ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል። ፈላስፋው በጥልቀት የተመለከታቸውን የእግዚአብሔር ህላዌነት፣ሥነ ምግባር፣ እውነት፣ በዓለም ላይ ስላሉ ሐይማኖቶች እሰጣገባ፣ ፍትህ፣ ስለ መለኮታዊውና ሰዋዊ ህግ፣ ማህበራዊ ኑሮና ዝመና የዘርዐ ያዕቆብ ፍልስፍናዊ ዕሳቤዎች ማተኮሪያ ናቸው፡፡
ዘርዐ ያዕቆብ የክርስትና ስሙ ሲሆን የዓለም ስሙ ወርቄ እንደሆነ በመጽሐፉ አስፍሯል። ከገበሬ ቤተሰብ ውስጥ የተገኘው ዘርዐ ያዕቆብ አክሱም ውስጥ በ1592 ዓ.ም ተወለደ፡፡ በኋለኛው የዕድሜ ክልል ውስጥ ግን ወደ ጎንደር ልዩ ስሙም እንፍራንዝ የተባለ ቦታ ነበር የኖረው፡፡ ዘርዐ ያዕቆብ መምህርነቱ፣ የትዳር ህይወቱና እንዲሁም የፍልስፍና መጽሐፉ ጭምር የጻፈው እንፍራንዝ ውስጥ መኖር ከጀመረ በኋላ ነው፡፡
ሌላው የዘርዐ ያዕቆብ ፍልስፍና ውስጥ ለዚህ ዘመን ሰው ጭምር ሊያስደንቀው የሚችል አንድ ጉዳይ አለ፡፡ ለሴቶች መብት መከበር፣ እኩልነትና ስለ ጋብቻ ያለው አተያይ ነው፡፡ ይህ እሳቤው እሱ ከኖረበት 17ኛው ክፍለ ዘመን እጅግ የቀደመና ለማህበረሰቡም እንግዳ የሆነ ሃሳብ ነው፡፡ የትዳር አጋሩ የሆነችው ሚስቱ መጀመሪያ አባቷን ጠይቆ፣ የአባቷን ይሁኝታ ካገኘ በኋላ፣ የእሷንም ፍቃድ ጠይቆ እንዳገባት በመጽሐፉ አስፍሯል፡፡ ዘርዐ ያዕቆብ በመጽሐፉ እንዳሰፈረው፤“…ሴት የሌለችው ወንድ ብቻውን ይኖር ዘንድ እንደማይገባው አወቅኩ…” በማለት፤ ሰዎች ተፈጥሯቸውን ክደው ሊኖሩ አይገባቸውም እያለ ይሞግታል፡፡ ሂሩትን፤ ምግባሯና ልባምነቷን መመዘኛ ማድረጉ፣ ጠንካራ የሆነ የፍቅር እምነት እንዳለው በመጽሐፉ ውስጥ አስፍሯል፡፡ ከአራት ዓመት በኋላም ከሚስቱ ከሂሩት ልጅ የወለደ ሲሆን ስሙም ሀብተ እግዚአብሔር እንደሚባል በመጽሐፉ ተጠቅሷል፡፡
በአጠቃላይ የዘርዐ ያዕቆብ ፍልስፍና የአንድ ማህበረሰብ መሰረት በምክንያታዊነት የተመራ የግለሰብ ጉዞ እንደሆነ ያሳያል፤ ስለዚህም የማህበረሰባዊ ለውጥ፣ አብሮ የመኖር ምስጢርና የማህበረሰባዊ ፍትህ በግለሰባዊ ነፃነትና ምክንያታዊ የሆነ ተፈጥሮ ላይ ይመረኮዛል፡፡ በተጨማሪም የዘርዐ ያዕቆብ ፍልስፍና የሁሉንም ሰዎች መሠረታዊ አኩልነት እንደ መነሻ አድርጐ ይቆጥራል፡፡
ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ
ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ሃገራችን ካፈራቻቸው ምጡቁ አሳብያን መካከል አንዱ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ምንም እንኳን እዚህ ምድር ላይ በህይወት የኖረው 31 ዓመታት ቢሆንም፤ ከዘመኑ የቀደመ፣ ምጡቅ አስተሳሰቡና ዕውቀቱ ግን ዛሬም ድረስ በብዙዎች የሚደነቅለት ታላቅ ምሁር ነው፡፡ የታሪክ ተመራማሪው ባህሩ ዘውዴ (ፕ/ር)፣ “Pioneers of Change in Ethiopia” በተሰኘው መጽሐፋቸው፤ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ የ20ኛው ክፍለ ዘመን የምሁራን ቁንጮና የለውጥ ፈር-ቀዳጅ በማለት በአድናቆት ገልጸውታል፡፡
ገብረ ሕይወት ጥልቅ ፍልስፍናዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እሳቤዎቹን ያሰፈረባቸው ሁለት መጻሕፍት አበርክቷል። እነዚህም “አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ” እና “መንግስትና የህዝብ አስተዳደር“ ይሰኛሉ። ገብረ ሕይወት “አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ” በተሰኘው መጽሐፉ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክና በታሪክ ውስጥ ስላጋጠሙ ፈተናዎች ይተነትናል፡፡ ኢትዮጵያን ለማዘመን የተደረጉ ሙከራዎችና ያጋጠሙ ፈተናዎችን ጭምር በዚህ መጽሐፍ ትልቅ ትኩረት ያገኙ ርዕሰ-ጉዳዮች ናቸው፡፡ ገብረ ሕይወት በመጽሐፉ የአንድ ማህበረሰብ የታሪክ አጻጻፍና ማህበረሰባዊ ዕድገት እንደማይነጣጠሉ ይገልጻል። በዚህ ላይ በመመርኮዝ ቅን የሆነ ልቦና፣ አለማዳላትና በቅንነት የታሪክ ሁነቶችን ለሌሎች ማሳወቅ፣ አንድን ማህበረሰብ የራሱን ማንነት የበለጠ እንዲረዳ አንደሚያደርጉ አጽንኦት ሰጥቶ ያሳስባል፡፡
የገብረ ሕይወት ሌላኛው ትልቁ ሥራው የ“መንግስትና የህዝብ አስተዳደር” ይሰኛል፡፡ ገብረ ሕይወት በዚህ መጽሐፉ ጥልቅ የሚባሉ የፖለቲካል-ኢኮኖሚ ፍልስፍናዊ ዕሳቤዎችን ያነሳል፡፡ ስለ ምርትና ምርታማነት፣ ኢምፖርትና ኤክስፖርት፣ ከሌሎች ሃገራት ጋር የሚደረጉ የንግድ ልውውጦች ሚዛን መጠበቅ አስፈላጊነት፣ የመንግስትና የህዝብ ግንኙነት…ባሉ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ አተያዮቹን በመጽሐፉ አስፍሯል፡፡
ለገብረህይወት የሀገር ነፃነት ማለት፣ የራስ መንግሥትን መመስረት ብቻ ሳይሆን እራስንም መቻል ነው፡፡ ገብረህይወት የ“መንግስትና የህዝብ አስተዳደር“ በተሰኘው መጽሐፉ እንዳሰፈረው፤ “እስቲ አሁን እኛ የኢትዮጵያ ህዝብ አርነት አለን ሊባል ነውን? አርነት ያለው ህዝብ ማለት እውነተኛ ትርጉሙ ለብቻው መንግሥት ያለው ህዝብ ማለት ብቻ አይደለም፡፡ ራሱንም የቻለ ህዝብ ማለት ነው እንጂ” ሲል ጥልቅ አተያዩን ይሰነዝራል፡፡
ሌላው በ“መንግስትና የህዝብ አስተዳደር” መጽሐፍ ውስጥ ገብረ ህይወት ካነሳቸው ትልልቅ ጥያቄዎች መካከል ስለ ስራ ምንነትና አስፈላጊነት አንዱ ነው፡፡ “…ማንኛውም ስራ እያደገ የሚሄደው ከተጀመረ በኋላ ነው:: ትልቅም ሀብት የሚሰበሰበው በጥቂት ሀብት ሲጀመር ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በአንድ አገር ውስጥ ከሰራተኛው በላተኛው ሲበዛ የተጀመረው ሁሉ እንደገና ስለሚጠፋ የበለጠ ስራ ለወደፊት መስራት አይቻልም:: በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ያለ አገር ህዝቡ እየበዛ ሲሄድ ምግቡ የማይበቃ እየሆነ ድህነት፣ችጋርና በሽታም እየሰፋ ይሄዳል፡፡ ስለዚህም የአንድ ሀገር ሀብት የሚያድገው ከሁሉ ነገር በፊት ሰራተኛው ከበላተኛው ያላነሰ ሲሆንና ማንኛውም ህዝብ ለኑሮው ከሚያስፈልገው አብልጦ ሲሰራ የበለጠ ሀብት ያገኛል” ይላል፡፡
ገብረ ህይወት ባይከዳኝ በትግራይ አድዋ ልዩ ስሙ ዘንጎይ መንደር ውስጥ ሰኔ 24 ቀን 1879 ዓ.ም ተወለደ፡፡ ገብረ ህይወት የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው በኦስትሪያ ሲሆን የከፍተኛ ትምህርቱን የተከታተለው ደግሞ በጀርመን አገር ነው፡፡ ከበርሊን ዩኒቨርሲቲ በህክምና ዶክተርነት ዲግሪውን የተቀበለው ገብረ ህይወት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሀኪም ከሆኑት ከዶ/ር ወርቅነህ እሸቴ (ሀኪም ወርቅነህ) ቀጥሎ የተገኘ ኢትዮጵያዊ ሀኪም ነው፡፡ ነገር ግን ገብረ ህይወት ከሐኪምነቱ በላይ የሚታወቀው በነጋድራስነቱ (የንግድ ማህበረሰብ የበላይ አስተዳዳሪነት) እና በጥልቅ ተመራማሪነቱ ነው። ገብረ ሕይወት በብዙ መልኩ ከዘመኑ የቀደመ፣ በጥልቅ አሳቢነቱና ዘርፈ ብዙ ዕውቀቱ የተደነቀ፣ ለህዝብና ለአገር ለውጥ ብዙ ራዕይ የነበረው ሰው ነው፡፡ አዳም ረታ አንጋፋው ደራሲ አዳም ረታ በፈጠራ የሥነ-ጽሑፍ ስራዎቹ ውስጥ የኢትዮጵያውያን የወል ማንነት፣ ዕሴት፣ ፍልስፍና እና ታሪክ ነክ ጉዳዮችን በጥልቀት በመዳሰስ የሚታወቅ የዘመናችን ደራሲና ፈላስፋ ነው፡፡ በተለይ በ2001 ዓ.ም በታተመው ‘እቴሜቴ የሎሚ ሽታ’፣ በ2006 ዓ.ም በታተመው ‘መረቅ’፣ በ2008 ዓ.ም በታተመው ‘የስንብት ቀለማት’ እና በሌሎቹም የፈጠራ ሥራዎቹ ጥልቅ ፍልስፍናዊ እሳቤዎቹን ያቀረበባቸው ሥራዎቹ ናቸው፡፡ አዳም ረታ በእነዚህ ኪናዊ ድርሰቶቹ ውስጥ እንደ ድህረ[1]ቅኝታዊነት (postcolonialism) ያሉ ፍልስፍናዊ እሳቤዎች በስራዎቹ ውስጥ በስፋት ይንፀባረቃል፡፡ እንደሚታወሰው ድህረ-ቅኝ ግዛታዊነት የቁም ፍቺው እንደሚያመለክተው ከቅኝ ግዛታዊነት (Colonialism) ቀጥሎ የሚመጣ ሥርዓት ማለት አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ የቅኝ ግዛታዊነት እሳቤዎችና ሌጋሲዎች በተዘዋዋሪ መንገድ በድህረ-ቅኝ ግዛታዊ ዘመን እንዴት እንደቀጠሉ የሚያትት እሳቤ ነው፡፡
በአዳም ረታ ሥራዎች ውስጥም ባዕድ የሆኑና የቅኝ አገዛዝ እሳቤዎች በትውልዱ አስተሳሰብ፣ የሕይወት ዘይቤና ተቋማት ውስጥ ጭምር እንዴት ሰርገው እንደገቡ አጉልቶ ያሳያል። በተለይ ተማርኩ የሚለው የሕብረተሰብ ክፍልን ይሞግታል፡፡ ጥልቅ ሂሶችንም ይሰነዝራል፡፡ ከዚህም አልፎ የራስን ወይም ሃገር በቀል ዕሴቶችን መመርመር፣ ወደ ራስ ጠልቆ መመልከት፣ ራስን ማወቅና በራስ እሴት ላይ የተመሰረተ ማህበራዊ ዕድገት እጅግ ወሳኝ መሆኑንም በድርሰቶቹ በስፋት ያስነበበ ደራሲና ፈላስፋ ነው፡፡
አዳም ረታ በ1950 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ነው የተወለደው፡፡ በትምህርት ዓለም በጂኦግራፊ የመጀመሪያ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ ሁለተኛ (የማስተርስ) ዲግሪውን ደግሞ በካናዳ ሀገር አግኝቷል። አዳም ረታ ዛሬ ላይ በህይወት ካሉ አንጋፋ ደራሲያንና አሳብያን መካከል አንዱ ሲሆን፣ በዚህ ዘመን ትውልድ እጅግ የሚወደድና የሚነበብ ደራሲም ነው፡፡
በአብርሃም ገብሬ