ኢትዮጵያ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ተጠቃሚ የምትሆንባቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች በጥቅምት ወር ይካሄዳሉ፦ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

You are currently viewing ኢትዮጵያ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ተጠቃሚ የምትሆንባቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች በጥቅምት ወር ይካሄዳሉ፦ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

AMN – ጥቅምት 1/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ተጠቃሚ የምትሆንባቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች በተያዘው የጥቅምት ወር በአዲስ አበባ እንደሚካሄዱ የመንግሥት ኮሙኒኬሽ አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሣ ገለጹ።

ሚኒስትር ዴኤታዋ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ፣ በጥቅምት ወር ከሚጠበቁት ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ኮንፈረንሶች መካከል ከረኃብ ነፃ የሆነ ዓለም የሚለው እና ከጥቅምት 26 እስከ 28 ቀን 2017 ዓም በአዲስ አበባ የሚካሄደው ኮንፈረንስ አንደኛው መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህ ኮንፈረንስ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ ትኩረት የሰጡት ኮንፈረንስ እንደሆነም አንስተዋል።

ዓለም አቀፍ ፈተና የሆነውን የረኃብ አደጋ በተደራጀ መልኩ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል በሚል የዓለም ሀገራት በጋራ የሚመክሩበት ጉባኤ በመሆኑም ሀገራት ልምዳቸውን የሚለዋወጡበት እንደሚሆን አመላክተዋል።

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ አስቻይ ሁኔታዎች መኖራቸውን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በሀገራችንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተመለከትነው ይህንኑ እንደሆነ አንስተዋል።

ዓለም አቀፍ ትብብርን የፖሊሲ ድጋፍንም ማድረግ እንደሚገባ በዚህ ኮንፈረንስ ላይ ይነሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

ከዚህም ባሻገር ዘላቂ የሆነ የምግብ ዋስትናን በዓለም አቀፍ ደረጃ መፍጠር በሚቻልባቸው ዘዴዎች ላይም ምክክር እንደሚደረግ አመላክተዋል።

ጉባኤው በሚቆይባቸው ሦስት ቀናት ውስጥም ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ ከ1 ሺህ 500 በላይ እንግዶች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።

በተለይም ደግሞ ሀገራት ረኃብን ለመዋጋት ምን ሠሩ በሚለው ዙሪያም ሪፖርት የሚያቀርቡበት እንደሆነም አንስተዋል።

ኢትዮጵያም በመድረኩ በበጋ ስንዴ፣ በአረንጓዴ አሻራ እና በከተማ ግብርና ያላትን ልምድ ታጋራለች ብለዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ መንግሥት፣ የግል ተቋማት፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ ሲቪክ ተቋማት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የጋራ ጥረት የሚያስፈልገው እንደሆነም በስፋት የሚነሣበት እንደሚሆንም ይጠበቃል ብለዋል።

የተቀናጀ ምልከታን ስለሚፈልግ እና በአንድ ዘርፍ ብቻ የሚሠራ ባለመሆኑ ውጤታማ የሆነ የማዕቀፍ ፖሊሲም ስለሚያስፈልገው ይህ ዓለም አቀፍ ፖሊሲ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

የካፍ ጉባኤ እና የአፍሪካ መከላከያ ጉባኤ በተከታታይ የሚደረጉ ሲሆን ኢትዮጵያ በተለይም አዲስ አበባ ከኮንፈረንስ ቱሪዝም ተጠቃሚ እንደምትሆን ነው የገለጹት።

ከአዲሱ ዓመት ጅምሮ የመስቀል እና ኢሬቻ አደባባይ በዓላት በስኬት እንደተጠናቀቁ የገለጹት ሚኒስተሯ፣ ለቀጣዮቹ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችም በቂ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

በፋሲል ጌታቸው እና ታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review