AMN – የካቲት 10/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መቋቋም የሚያስችሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማ ስራዎች እያከናወነች መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።
ስምንተኛው የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም “ከእመርታ ወደ ብልጽግና፤ የአፍሪካን ቀጣናዊ የእሴት ሰንሰለቶች አቅም ማጠናከር” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የቢዝነስ ፎረሙ በአፍሪካ የቁም እንስሳት፣ ግብርና እና ፋርማሲዩቲካል ዘርፎች ቀጣናዊ የእሴት ሰንሰለት እና ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ልማት ላይ ያተኮረ ነው፡፡
ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በምርቶች ላይ እሴት መጨመር የአፍሪካን ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ያሳድጋል።
ለኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ስራ ዕድል ፈጠራ ያለውን ፋይዳም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅምን ከማሳደግ ረገድ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዘግቧን ጠቅሰው፤ በአጭር ጊዜ ምርታማነትን በመጨመር በስንዴ ምርት ራሷን መቻሏን ጠቁመዋል።
በአፍሪካ የማምረት አቅምን ለማሳደግ ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባም ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በርካታ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ለኢንቨስትመነት ፍሰት ምቹ ሁኔታ መፍጠሯን ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል ።