AMN – ጥር 19/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ለጀመረችው የዲጂታል ሽግግርና ፈጠራን መሰረት ያደረገ የኢኮኖሚ እድገት ከጣሊያን መንግሥት የ585 ሚሊየን ብር ድጋፍ አገኘች።
የድጋፍ ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ እና የጣልያን የከፍተኛ ትምህርት እና ምርምር ሚኒስትር አና ማሪያ ፈርመውታል።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ የጣሊያን መንግሥት ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ የኢትዮጵያን የዲጂታል አገልግሎት ለማጠናከር ያግዛል።
የድጋፍ ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት የቆየ ታሪካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ጂኦፖለቲካል ያላት ጠንካራ ሚና የጋራ መገለጫ መሆኑን ይጠቁማል ብለዋል።
ድጋፉ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ግቦችን ከማሳካት ባለፈ የሁለቱን ሀገራት ትብብር የሚያሳድግ መሆኑን አንስተዋል።
የጣሊያን የከፍተኛ ትምህርት እና ምርምር ሚኒስትር አና ማሪያ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የጣሊያን አጋር በመሆኗ በጋራ እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የውሀ አስተዳደር፣ የግብርና ቴክኖሎጂ፣ ሳይንስና ኢኖቬሽን ዘርፎች በጋራ የምንሰራባቸው የጋራ ራዕዮቻችን ናቸው ብለዋል።