AMN – ታኅሣሥ 18/2017 ዓ.ም
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) በኢትዮጵያ የሚያደርገውን የማህበራዊ ዘርፍ ድጋፍ እንደሚያጠናክር አስታወቀ።
ባለስልጣኑ ‘ሂውማን ብሪጅ’ ከተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ያገኘውን የህክምና መገልገያ ቁሳቁስ በዋና ጸሃፊው ወርቅነህ ገበየው (ዶ/ር) አማካኝነት ለነጌሌ ቦረና ጠቅላላ ሆስፒታል ድጋፍ አድርጓል።
ድጋፉም ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የህክምና አልጋና ፍራሽ፣ የአካል ድጋፍ እንዲሁም የላቦራቶሪ መሳሪያዎች መሆናቸውም ተገልጿል፡፡
በኢጋድ የኢትዮጵያ ተጠሪ አቶ አበባው ቢሆነኝ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት ባለስልጣኑ አባል አገራቱን በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፎች ለማሳደግ ገዘፍ ያሉ ስራዎችን እያከናወነ ነው።
በተለይም በኢትዮጵያ የማህበራዊ ዘርፍ በርካታ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው በምስራቅ ቦረና ዞን ለነጌሌ ጠቅላላ ሆስፒታል ያደረገው ድጋፍም የዚሁ አካል መሆኑን ተናግረዋል።
ባለስልጣኑ ከዚህ ቀደምም ለአርባ ምንጭ፣ ለአርሲ ሆስፒታል እንዲሁም በአማራ ክልል ለሚገኙ የተለያዩ ሆስፒታሎች የተሻለ የህክምና አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችላቸውን ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
ባለስልጣኑ በኢትዮጵያ እና በሌሎች አባል አገራት ድንበር አካባቢዎች የጤናውን ዘርፍ ለማጠናከር የሚያስችል ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።
እንደ አቶ አበባው ገለጻ ባለስልጣኑ በጤናና በህብረተሰብ አገልግሎት ስራው ወረርሽኝንና ድንበር ተሻጋሪ በሽታዎችን ለመከላከል ጥረት እያደረገ ነው።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አብዱልቃድር ገልገሎ (ዶ/ር)፣ የጤና ዘርፉ በርካታ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ የግል እና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ድጋፍን ይፈልጋል ብለዋል።
በኢጋድ በኩል የተደረገው ድጋፍም በሆስፒታሉ የሚስተዋለውን የህክምና መገልገያ ቁሳቁስ ጉድለት ለመሙላት የሚያግዝ መሆኑንም አስረድተዋል።
የተደረገው ድጋፍ የክልሉ መንግስት የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል የሚያደርገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ቦኮና ጉታ (ዶ/ር) ናቸው።
ሆስፒታሉ በህክምና ግብዓት እጥረት ምክንያት ለተገልጋዮች የተሻለ ህክምና ለመስጠት በመቸገሩ ተገልጋዮች ለእንግልት ሲዳረጉ መቆየታቸውን አስታውሰው ድጋፉ ይህንን ችግር እንደሚያቃልለው ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ሲሆን ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የምስራቅ ቦረና ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብዱራዛቅ ሁሴን፣ ከተቋቋመ 50 ዓመታትን ያስቆጠረው የነጌሌ ቦረና ሆስፒታል በርካታ ችግሮች እንዳሉበት ጠቅሰዋል።
የሆስፒታሉ ተገልጋዮች አርሶ እና አርብቶ አደሮች መሆናቸውን ጠቅሰው ድጋፉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን የሚያቃልል መሆኑን ማመልከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የነጌሌ ቦረና ከተማ ነዋሪው ሼህ ከድር አብዱራህማንም ለሆስፒታሉ የተደረገው ድጋፍ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ለቆዩት የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተስፋ መሰነቃቸውን ተናግረዋል።