ሊገባደድ ጥቂት ጨዋታዎች የቀሩት የ2024/25ቱ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር በፕሪሚየር ሊግ ታሪክ 33ኛ የውድድር ዘመን ነው። የባለፈው የውድድር ዓመት ወደታችኛው እርከን የወረዱትን ሉቶን ታውንን፣ በርንሌይን እና ሼፊልድ ዩናይትድን ተክተው ከሻምፒዮንሺፑ (ታችኛው እርከን) ያደጉት ሌስተር ሲቲ፣ ኢፕስዊች ታውን እና ሳውዝሃምፕተን አካትቶ ነበር ውድድሩ መካሄድ የጀመረው፡፡ ሌስተር ሲቲ እና ሳውዛምፕተን ወደ ዘንድሮው ውድድር ዓመት ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ የተመለሱ ሲሆን ኢፕስዊች ታውን እግር ኳስ ክለብ ግን ከሃያ ሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ ነበር የተመለሰው።
ይህ የውድድር ዘመን ከፊል አውቶሜትድ ኦፍሳይድ ቴክኖሎጂን ሲጠቀም የመጀመርያው ሲሆን ቴክኖሎጂውን ለመተግበርም የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በአንድ ድምፅ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር ወደ ትግበራ የተገባው፡፡ ከጨዋታ ውጪ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር ይረዳል የተባለለት ይህ ቴክኖሎጂ በአምስተኛው ዙር በኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫ ውድድር ላይ ሙከራ ከተደረገለት በኋላ ሲሆን፤ ወደ ሙሉ ስራ የገባው የማንቸስተር ሲቲው ኢትሃድ ስታዲየም ደግሞ ቴክኖሎጂውን በይፋ የተጠቀመው የመጀመሪያው ስታዲየም ሆኗል፡፡
እየተገባደደ ባለው የውድድር ዓመት በውጤት ማጣት ምክንያት አሰልጣኞች ስንብት ገጥሟቸዋል፡፡ የመጀመሪያው ተሰናባች አሰልጣኝ ደግሞ በውጤት ማጣት ውስጥ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ ሲሆን፤ በዌስትሀም ዩናይትድ 2ለ1 ሽንፈትን ተከትሎ የቀድሞ አሰልጣኙን ኤሪክ ቴን ሀግን አሰናብቶ ፖርቱጋላዊውን አሰልጣኝ ሩበን አሞሪምን ቀጥሯል፡፡
የሁለተኛው የአሰልጣኝ መልቀቅ የተሰማው ደግሞ በህዳር ሲሆን፤ ወደታችኛው የውድድር እርከን የወረደው ሌስተር ሲቲ በቼልሲ 2ለ1 በሜዳው መሸነፉን ተከትሎ ስቲቭ ኩፐርን ሲያባርር ነበር። ክለቡ በወቅቱ 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ ከፍ ብሎ የተቀመጠ ሲሆን በውድድር ዘመኑ ስድስተኛ ሽንፈቱን አስተናግዶ በ12 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው 2 ጨዋታዎችን ብቻ ነበር። እ.ኤ.አ. ከቀናት በኋላም ሆላንዳዊውን አሰልጣኝ ሩድ ቫን ኒስቴልሮይን ይቅጠር እንጂ ከመውረድ ሳያተርፈው ቀርቷል፡፡
ዎልቨርሃምፕተን ዋንደርስ በሜዳው በኢፕስዊች ታውን 2ለ1 ከተሸነፈ በኋላ ዋና አሰልጣኝ ጋሪ ኦኔይልን አሰናበተ። አሰልጣኛቸውን ሲያሰናብቱም በ16 ጨዋታዎች 11ኛ ሽንፈታቸውን ያስተናገዱ ሲሆን፤ በደረጃም 19ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ከወራጅ ቀጠና አራት ነጥብ ርቀት ላይ ብቻ ነበር የሚገኙት፡፡
በዚሁ ቀን ሌላኛው ወራጅ ቀጠና ላይ የሚገኘው ሳውዛምፕተን በቶትንሃም ሆትስፐር 5ለ0 በሜዳው ከተሸነፈ በኋላ አሰልጣኙ ራስል ማርቲን ተሰናብተው በኢቫን ጁሪች ተተክተዋል። ከላይ ከጠቀስናቸው ክለቦች በተጨማሪ ዌስትሃምና ኤቨርተንን ጨምሮ በአጠቃላይ ሰባት ክለቦች አሰልጣኞቻቸውን ያሰናበቱበት ዓመት ነበር፡፡
በዓመቱ በቶትንሃም ሆትስፐር 4ለ0 የተሸነፈበትን ጨዋታ ጨምሮ ባደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች ያለምንም ድል የዘለቀው የአምናው ሻምፒዮን ማንቸስተር ሲቲ ከ2008 ወዲህ አራት ተከታታይ የሊግ ሽንፈቶችን አስተናግዷል። ኖቲንጋሃም ፎረስት ብራይተንን ሰባት ለባዶ ያሸነፈበት ጨዋታ ደግሞ ከፍተኛ ግቦችን ያስተናገደው ጨዋታ ሆኖ ተመዝግቧል።በወርሃ የካቲት ሳውዝሃምፕተን ከሜዳው ውጪ በቶትንሃም ሆትስፐር 3ለ1 ሽንፈትን አስተናግዶ በአንድ ዓመት ከፍተኛ ሊግ ከቆየ በኋላ ወደ ታችኛው ሻምፒዮና የወረደ የመጀመሪያው ቡድን ሲሆን፣ በ 33 ጨዋታዎች 11 ነጥብ ብቻ በመያዝ በፕሪሚየር ሊግ ታሪክ 7 ጨዋታዎች እየቀረው በመውረድ የመጀመሪያው ቡድን ሆኗል።
ሌስተር ሲቲ በሜዳው በሊቨርፑል 1ለ0 ሽንፈትን ተከትሎ ወደ ታችኛው ዲቪዚዮን የወረደ ሁለተኛው ቡድን ሆኗል። ወደ ፕሪሚየር ሊግ በመጣበት ዓመት የወረደው ሌስተር ሲቲም በኒውካስል ዩናይትድ 3ለ0 ከተሸነፈ በኋላ በሜዳው ባደረጋቸው 9 ተከታታይ ጨዋታዎች ጎል ሳያስቆጥር የመጀመሪያው ክለብ መሆን ችሏል። በተቃራኒው የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ከቀሪ አምስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ የሚያስፈልገው ሊቨርፑል ዌስትሃም ዩናይትድን 2ለ1 በማሸነፍ ለ2025/26 የአውሮፓን ቻምፒየንስ ሊግ ማለፍ የቻለ የመጀመሪያው ቡድን ሆኗል።
ማንቸስተር ዩናይትድ በዎልቨርሃምፕተን ዋንደርስ በኦልድትራ ፎርድ 1ለ0 ሽንፈትን አስተናግዶ በውድድር ዓመቱ 15ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደ ሲሆን፣ በፕሪሚየር ሊጉ በአንድ የውድድር ዘመን 14 ሽንፈትን በማስመዝገብ ይዞት የነበረውን የባለፈውን የውድድር ዘመን መጥፎ ታሪክ አሻሽሎታል።
በሻምፒዮንሺፑ እየተሳተፉ የሚገኙት ሊድስ ዩናይትድና በርንሌ እንደዚሁ በ44ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ተጋጣሚዎቻቸውን ማሸነፋቸውን ተከትሎ ከታችኛው እርከን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማደጋቸውን አረጋግጠዋል። በሜዳው ስቶክ ሲቲን የገጠመው ሊድስ ዩናይትድ 6 ለ 0 በሆነ ሰፊ ልዩነት አሸንፎ ሲሆን፣ ማለፉን ያረጋገጠው በጀርመናዊው አሰልጣኝ ዳንኤል ፋርክ የሚመራው ሊድስ ዩናይትድ ሊጉ ሊጠናቀቅ ሁለት ጨዋታ እየቀረው በ94 ነጥብ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ተመልሷል። በተመሳሳይ በርንሌይ ሼፍልድ ዩናይትድን 2 ለ 1 በማሸነፍ መመለሱን አረጋግጧል። በርንሌይ ከሊድስ እኩል 94 ነጥብ በመሰብሰብ በግብ ክፍያ ተበልጦ ወደ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የተመለሰበትን ውጤት አስመዝግቧል።
የሊግ እግር ኳስ ተንታኝ አሌክስ ኬብል የዓመቱን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አስመልክቶ ባስነበበው ጽሑፍ እንዳሰፈረው፣ በዚህ ዓመት ክለቦች ለውጤታማነት ይዘውት የመጡት አንድ ስልት የቆሙ ኳሶች ላይ አትኩሮ መሰራት ነው፡፡ በዚህም አንዳንድ ክለቦች አስገራሚ ውጤትም አምጥተውበታል ይላል፡፡ በአስረጅነትም የአርሰናል እግር ኳስ ክለብን ይጠቅሳል፡፡ በዘመናዊ እግር ኳስ በኃያላኑ መካከል ያለው ልዩነት የመርፌ ቀዳዳ ያህል እየሆነ መጥቷል። ይህንን ከጊዜ እና ቦታ ጋር አዋህዶ መጠቀም የብልህ አሰልጣኝ ውሳኔ ነው። የእንግሊዙ አርሰናል እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኙ ኒኮላስ ጆቬር ቅጥርም ከዚህ አንጻር የሚታይ ነው፡፡
ኒኮላስ ጆቬር እ.ኤ.አ በ2021 አርሰናልን ከተቀላቀለ በኋላ መድፈኞቹ ከማዕዘን ከሚሻገሩ ኳሶች 48 ግቦችን አስቆጥረዋል። ይህም በአማካይ ከ16 ነጥብ 4 የማዕዘን ምቶች አንዱን ወደ ጎል ይቀይራሉ ማለት ነው። በዘንድሮው ዓመትም የአርሰናል እግር ኳስ ክለብ ከቆሙ ኳሶች 14 ግቦችን አስቆጥረዋል ይላል እግር ኳሳዊ ትንታኔዎችን የሚሠጠው የኦብታ መረጃ።
ይህን መረጃ እስካጠናቀርንበት ጊዜ ድረስ የፕሪሚየር ሊግ ድረ-ገፅ ላይ የወጣ ቁጥራዊ መረጃ እንደሚያሳየው የሊቨርፑሉ ሞሃመድ ሳላህ በ27፣ የማንቸስተር ሲቲው ኤርሊንግ ሃላንድ በ21 እና የኒውካስትሉ አሌክሳንደር ኢሳክ 19 ግቦችን በማስቆጠር የሊጉን ግብ አስቆጣሪነት እየመሩ ይገኛል።
በእግር ኳሱ ዓለም እያስመዘገበ ያለውን ስኬት ተከትሎ ከትውልድ ሀገሩ አልፎ አፍሪካን እያስጠራ ያለው የወቅቱ ስመ ጥር የእግር ኳስ ጠቢብ ሞሐመድ ሳላህ በዘንድሮው ዓመት እያሳየ ባለው እንቅስቃሴም የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች አሸናፊነትን እንደሚያገኝ አያጠራጥርም ይላል ተንታኙ አሌክስ ኬብል፡፡
ለ30 ዓመታት ከፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ርቆ ከነበረው ሊቨርፑል ጋር ከአምስት ዓመት በፊት የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ አሸንፎ የነበረው ሳላህ አሁን ላይ ሊቨርፑል 20ኛውን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ለማንሳት ከጫፍ በደረሰበት ሂደት ውስጥ ትልቁን አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል። በዚህ የውድድር ዓመት የሊጉ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ ለመጨረስ ከጫፍ ደርሷል፡፡ በውድድር ዓመቱ ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች በርካታ ክብረወሰኖችን እየተጋራ ይገኛል። በፕሪሚየር ሊጉ በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ የጎል አስተዋፅኦ በማድረግ ከአለን ሺረር እና ከአንድሪው ኮል በመቀጠል ሦስተኛው ተጫዋች ሆኗል፡፡
የብዙዎች ግምት የነበረው የሊጉ ዋንጫ አሸናፊነት ከማንቸስተር ሲቲና ከአርሰናል አያልፍም የሚለውን ቅድመ ግምት ፉርሽ ያደረገው የሊቨርፑል እግር ኳስ ክለብ ሊጉን በ79 ነጥብ እየመራ ከተከታዩ አርሰናል ያለው የነጥብ ልዩነትም 12 አድርሷል፡፡ አሸናፊነቱንም ለማረጋገጥ ነገ ከቶትንሃም ጋር ከሚያደርገው ጨዋታ ላይ አንድ ነጥብ ብቻ በቂው ነው፡፡ አሰልጣኝ አርኔ ስሎት ደግሞ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ በመጀመሪያ የውድድር ዘመን ዋንጫ ማንሳት የቻሉ አምስተኛው አሰልጣኝ ሊሆኑ ተቃርበዋል።
በሳህሉ ብርሃኑ