የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን እና የአህጉሪቱ ትልቅ ውድድር የሆነው አፍሪካ ዋንጫ ተመስርተው በሁለት እግራቸው እስኪቆሙ ድረስ ኢትዮጵያ የነበራት ድርሻ በደማቅ ቀለም የተጻፈ ነው፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የአፍሪካ አገራት በጨዋታው እንዲሳተፉ በማድረግ፣ የመጀመሪያውን የካፍ መተዳደሪያና የውድድር ደንቦች ማዘጋጀትን ጨምሮ ለአስራ አራት አመት ያህል ካፍን በፕሬዝዳንትነት እስከመምራት የኢትዮጵያ ሚና ላቅ ያለ ነው፡፡
ለ46ኛው ጠቅላላ የካፍ ጉባኤ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የእግር ኳሱ መሪዎችም ያረጋገጡት ይህንኑ ሀቅ ነው፡፡ የዓለም እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) ምስረታ እና ለአፍሪካ አንድነት ትልቅ ሚና መጫወቷን የገለጹትም ለዚሁ ነው። ጂያኒ ኢንፋንቲኖ እግራቸው አዲስ አበባን እንደረገጠ የተናገሩት የመጀመሪያው ሀሳብ፣ “ወደ ቤቴ በመምጣቴ እጅግ ደስተኛ ነኝ፡፡ ወደ ቤተሰቦቼ እንደመጣሁ እስኪሰማኝ ድረስ ለተደረገልኝ አቀባበል አመሰግናሁ” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ አያይዘውም “ሁሌም ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ የአፍሪካ ቤት እንዳለሁ ይሰማኛል” ያሉት ኢንፋንቲኖ፣ ወደ ኢትዮጵያ በድጋሚ በመምጣታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ2029 የሚካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ የማዘጋጀት አቅም አላት ያሉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የ2029ኙን አፍሪካ ዋንጫ እንድታዘጋጅ በይፋ ጠይቀዋል። የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሙትሴፔ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ያቀረበችውን ጥያቄ ካፍ ከኮሚቴው ጋር እንደሚመክርበት ገልጸው፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ጥያቄ በማቅረቧ ደስተኛ ነኝ ብለዋል፡፡
አክለውም “ኢትዮጵያ የካፍ መሥራች ሆና ለረጅም ዓመት ውድድሩን አላዘጋጀችም። ይህ መሆን አልነበረበትም። አሁን ጊዜው ጥሩ ይመስለኛል። እግር ኳስን ለማሳደግ ምንም ለማድረግ ዝግጁ የሆነ መሪ አላችሁ” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ እንድታዘጋጅ በካፍ ስብሰባ ላይ የጠየቁ ሲሆን፣ “አስራ አንድ ስቴዲየም ለመገንባት እየሰራን እንገኛለን፡፡ ኢትዮጵያ ካፍ እንዲመሰረት እና የአፍሪካ እግር ኳስ እንዲያድግ ትልቅ ሚና ተወጥታለች። የ2029 አፍሪካ ዋንጫ እንድታዘጋጅ እንጠይቃለን’’ ብለዋል፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ የኢትዮጵያን የአፍሪካ ዋንጫ መስተንግዶ ጥያቄ እንዲቀበል የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴም በጉባዔው ላይ ንግግር ባደረጉት ወቅት ኢትዮጵያ የ2029ኙን የአፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ አቅሙም ልምዱም እንዳላት ጠቅሰው፣ ጉባዔው ይሁንታ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
መንግስት በአገሪቷ የሚገኙ ግንባታቸው የተጀመሩ ስታዲየሞችን የማጠናቀቅ ስራ እንደሚሰራ የተናገሩት ደግሞ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ ናቸው። አብዛኞቹ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ያስታወሱት ሚኒስትሯ፣ የአፍሪካ የእግር ኳስ የበላይ አካል (ካፍ) ይሁንታውን የሚሰጥ ከሆነ ከ5 ዓመት አስቀድሞ ስታዲየሞቹን የማጠናቀቅ ስራ እንደሚሰራ አሳውቀዋል። ከስቴዲየሞቹ ባሻገርም ተተኪ ስፖርተኞች የሚወጡባቸው ትንንሽ ሜዳዎች ታሳቢ እንደሚደረጉና ውድድሩን ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉ ተጨማሪ የመሰረተ ልማት ስራዎች ላይ ትኩረት እንደሚደረግም ማብራሪያ ሰጥተዋል ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ።
የካፍ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱም ይዞት የመጣው እድል ቀላል አለመሆኑንና በተለይም ኢትዮጵያ መንግስትና ስፖርቱን የሚመሩ አካላት እግር ኳሱን ለማሳገድ ያላቸውን ተነሳሽነት ካፍ የተመለከተበት እንደሆነና ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት የሚገልጹት ደግሞ በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህሩ አሰግድ ከተማ ናቸው፡፡
እሳቸው እንደሚሉት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት መጠየቋ ተገቢ እንደሆነና ይሁንታ አግኝቶም ዕድል ከተገኘም ይዞት የሚመጣው ትሩፋት ቀላል እንደማይሆን አስረድተዋል፡፡ በተለይ የስፖርት መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት በመንግስት በኩል ያለው ከፍተኛ ተነሳሽነት ከዚህም በላይ እንዲያድግና በስፖርቱ ለዓመታት የዘለቁት ችግሮችን ለማቃለል ድርሻው ከፍተኛ እንደሆነም አብራርተዋል። የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ በትራንስፖርት አቅርቦት፣ በፀጥታና ደህንነት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ብቁ ብትሆንም በዋናነት የጐደሉት ተጨማሪ የመሰረተ ልማት ስራዎችና፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታድየሞች በመሆናቸው እድሉን ብታገኝ እነዚህንም ለማስተካከል እንደምትሰራ ነው፡፡
የፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በበኩላቸው የአፍሪካ እግር ኳስ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻልና እድገት እያሳየ ነው ብለዋል፡፡ ፊፋ በወጣቶች ልማት፣ በወንድና ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ግንባታ፣ በወጣቶችና ክለቦች ውድድር ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን ኢንፋንቲኖ ኢትዮጵያም መሪዎቿ ለስፖርቱ እድገት እያሳዩት ያለው ቁርጠኝነት ሊመሰገን እንደሚገባው በጉባኤው ላይ ገልጸዋል፡፡
ከቀድሞ አፍሪካውያን እግር ኳስ ተጫዋች ኮከቦች መካከል ናይጄሪያዊው ጄጄ ኦካቻ፣ ካሜሩናዊው ሳሙኤል ኤቶ፣ ሴነጋላዊው አልሐጂ ዲዩፍ እና ካሉሺያ ቡዋልያም አዲስ አበባ የተገኙ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫውን ለማሰናዳት ያሳየችው ፍላጎት ተገቢ መሆኑንና አቅሙም እንዳላት በቆይታቸው መታዘባቸውን ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ በኢትዮጵያ መካሄዱ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ከማነቃቃት ባሻገር ለገጽታ ግንባታ እና ቱሪዝም ዘርፍ መነቃቃት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረውም የስፖርት ሳይንስ መምህሩ አሰግድ ከተማ ያስረዳሉ። እንደ አፍሪካ ዋንጫ ያሉ ትላልቅ ዝግጅቶች ጎብኚዎችን ወደ ዝግጅቱ በመሳብ እና በመድረሻው ላይ ዓለም አቀፍ ትኩረትን ከመሳብ አንፃር ኢትዮጵያን ይጠቅማል። ከእንደዚህ አይነት የአጭር ጊዜ ጥቅማጥቅሞች በተጨማሪ የረጅም ጊዜ የቱሪዝም ልማትን ከኢኮኖሚያዊ እስከ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ማበረታቻ ሊሆን ይችላል። ቱሪስቶች ከኢትዮጵያውያን፣ ከተፈጥሮ እና ባህል ጋር በተሻለ ሁኔታ እንዲገናኙ ያስችላቸዋል የሚል ነው የመምህሩ አስተያየት።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ እግር ኳስ ላይ ጉልህ አሻራ ከማኖሯ በተጨማሪ ህዝቡ ለእግር ኳስ ያለው ፍቅር የሚታወቅ ነው የሚሉት መምህሩ አሰግድ ከተማ፣ በመሆኑም ኢትዮጵያ አፍሪካን በትልቅ ደረጃ የመወከል አቅም እንዳላት አንስተዋል፡፡ እንደዚሁም የአፍሪካ ዋንጫን ማሰናዳት ከቻለች ደግሞ ኢትዮጵያን ለዓለም መድረክ ለማስተዋወቅ፣ ከስፖርት ጋር የሚሰሩ የዓለም አቀፍ ተቋማትም በስፖርት መሰረተ ልማትና አካዳሚዎችን በኢትዮጵያ ለመስራት በር ከፋች እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡
እግር ኳስ ከስፖርት ባሻገር አገር የማስተዋወቂያ መንገድ በመሆኑም በዘርፉ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል መምህር አሰግድ፡፡ በሌላም በኩል የስፖርቱን አስተዳደር ሁለገብ አቅም እንደሚያሳድግና የስፖርት መሰረተ ልማቶች እንዲስፋፉና የስፖርት እድገትን ለማቀላጠፍ ድርሻው ቀላል አይደለም በማለት ሀሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡
ለአፍሪካ ዋንጫው ዝግጅት ደረጃቸውን የጠበቁ ስድስት ስቴዲየሞችን እና በርካታ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላት መገንባት የቻለችው አይቮሪኮስትም ለዚህ ጥሩ ማሳያ ተደርጋ ትጠቀሳለች፡፡ እንደዚሁም እንደ ደቡብ አፍሪካ ያሉ አገራት የአፍሪካ ዋንጫውን የማዘጋጀት አጋጣሚ ተጠቅመው በርካታ ስቴዲየሞችን መገንባት ሲችሉ በሂደትም ብዙ ሚሊዮን ዶላሮችን የሚያስገኙ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማዘጋጀት ችለዋል፡፡
ከ2029 የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት እስካሁን 13 አገራት የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ስለመጠየቃቸው የካፍ መረጃ ያሳያል፡፡ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የተካሄደው 46ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ሲጠናቀቅ የጠቅላላ ጉባዔው ሚና፣ የካፍ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዓመታዊ ስብሰባዎችና የካፍ ኤክስፖን ጨምሮ በካፍ መተዳደሪያ ደንብ ላይ የሚገኙ የተለያዩ አንቀጾች ላይም ማሻሻያ ተደርጓል።
እንደዚሁም የአፍሪካን እግር ኳስ ልማት እና እድገት ማጠናከር፣ አፍሪካ በዓለም እግር ኳስ ያላትን ውጤታማነት ማሳደግ፣ የስፖርት መሰረተ ልማቶች ግንባታ፣ የካፍ አባል አገራት ለእግር ኳስ ልማት የሚመድቡትን የፋይናንስ መጠን ማሳደግ በጉባዔው የተነሱ ዋና ዋና ሀሳቦች ናቸው፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ